ዘኍል 11:1-15
ዘኍል 11:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡም በክፋት በእግዚአብሔር ፊት አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ በእነርሱ ላይ ነደደች፤ ከሰፈሩም አንዱን ወገን በላች። ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እሳቲቱም ጠፋች። ከእግዚአብሔርም ዘንድ በእነርሱ ላይ እሳት ስለ ነደደች የዚያ ስፍራ ስም “መካነ ውዕየት” ተብሎ ተጠራ። ከእነርሱም ጋር የተቀላቀሉ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤልም ልጆች ተቀምጠው እንዲህ እያሉ አለቀሱ፥ “ሥጋ ማን ያበላናል? በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዳቦውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት ቍንዶ በርበሬውንም እናስባለን። አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዐይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም” አሉ። መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፤ መልኩም እንደ በረድ ነጭ ነበር። ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፤ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፤ እንጎቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጎቻ ነበረ። ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር። ሙሴም እያንዳንዳቸው በየወገናቸው በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ እግዚአብሔርም እጅግ ተቈጣ፤ ነገሩም በሙሴ ፊት ክፉ ሆነ። ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ለምን በአገልጋይህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስን አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሁሉ ሕዝብ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ፦ ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቅፍ በብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወይስ ወለድሁትን? በፊቴ ያለቅሳሉና፦ የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከየት አለኝ? እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ይቅርታን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።”
ዘኍል 11:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ስለ ደረሰባቸው ችግር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ማጕረምረማቸውን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) እሳት በመካከላቸው ነደደች፤ ከሰፈሩም ዳርቻ ጥቂቱን በላች። ሕዝቡ ወደ ሙሴ ጮኸ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እሳቲቱም ጠፋች። ከዚህ የተነሣም የቦታው ስም፣ “ተቤራ” ተባለ፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እሳት በመካከላቸው ነዳለችና። ድብልቁ ሕዝብ ሌላ ምግብ ጐመጀ፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ያጕረመርሙ ጀመር፤ “ምነው የምንበላው ሥጋ ባገኘን ኖሮ! በግብፅ ያለ ምንም ዋጋ የበላነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኵርቱ ትዝ ይለናል። አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቷል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!” መናው እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ የሙጫ መልክ ነበረው። ሕዝቡ ተዘዋውሮ በመልቀም በወፍጮ ከፈጨ ወይም በሙቀጫ ከወቀጠ በኋላ በምንቸት ይቀቅለው ወይም ይጋግረው ነበር፤ ጣዕሙም በወይራ ዘይት የተጋገረ ያህል ይጣፍጥ ነበር። ጤዛው ሌሊት በሰፈር ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም እንዲሁ ይወርድ ነበር። ሙሴ፣ ሕዝቡ ሁሉ በየቤተ ሰቡ፣ በየድንኳኑ ደጃፍ ሆኖ ሲያለቅስ ሰማ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እጅግ ተቈጣ፤ ሙሴም ተጨነቀ። እርሱም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “እንዲህ ያለውን መከራ በባሪያህ ላይ ለምን አመጣህ? የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም የጫንህብኝስ ምን አስቀይሜህ ነው? ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስሁት እኔ ነኝን? እኔስ ወለድሁትን? ታዲያ ሞግዚት ሕፃን እንደምትታቀፍ በክንዴ ታቅፌ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው የምትነግረኝ ለምንድን ነው? ለዚህ ሁሉ ሕዝብስ ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? ሁሉም ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን’ እያሉ ያለቅሱብኛል። እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርገኝ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”
ዘኍል 11:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች። ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እሳቲቱም ጠፋች። የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ስለነደደች የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው። በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ። መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር። ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ። ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር። ሙሴም ሕዝቡ በወገኖቻቸው፥ ሰው ሁሉ በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም ተቈጣ። ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፦ ለምን በባሪያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ፦ ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቅፍ በብብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወለድሁትንስ? በፊቴ ያለቅሳሉና፦ የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት እወስዳለሁ? እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።
ዘኍል 11:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤላውያን ስለ ደረሰባቸው ችግር ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረም ጀመሩ፤ እግዚአብሔርም የማጒረምረም ጩኸታቸውን ሰምቶ እጅግ በመቈጣት የሚባላ እሳት ላከባቸው፤ ያም እሳት ከሰፈሩ አንዱን ክፍል አወደመ። ሕዝቡም ያማልዳቸው ዘንድ ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እሳቱም ተገታ። የእግዚአብሔር እሳት በዚያ ስፍራ በመካከላቸው ስለ ነደደ ያ ስፍራ “ታብዔራ” ተብሎ ተጠራ። ከእስራኤላውያን ጋር የሚጓዙ የውጪ አገር ሰዎች ሥጋ ለመብላት የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ማልቀስ ጀመሩ፦ “የምንበላውን ሥጋ ከየት እናገኛለን! በግብጽ ሳለን ምንም ዋጋ ሳንከፍል የፈለግነውን ያኽል ዓሣ እንበላ እንደ ነበረ እናስታውሳለን፤ በዚያ ሳለን እንበላ የነበረውን ዱባ፥ (ኪያር) ሀብሀብ (በጢኽ)፥ ኲራት (ድንች መሳይ ምግብ) ቀዩንና ነጩን ሽንኩርት፥ አሁን ግን ሰውነታችን ደርቆ ኀይላችን ደከመ፤ የምንመገበው ምንም ነገር የለም፤ በየቀኑ ከዚህ መና በቀር ሌላ የምናየው የለም።” መና እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ እንደ ሙጫ ነጣ ያለ ቢጫ መልክ ነበረው፤ ሰዎቹም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፤ በወፍጮም ይፈጩት ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ያፈሉትና ይጋግሩት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ ቂጣ ነበር፤ ሌሊት ጠል በሰፈሩ ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም አብሮት ይወርድ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ በየቤተሰባቸው ቆመው ሲያለቅሱ ሙሴ ሰማቸው፤ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጥቶ ስለ ነበረ ሙሴ በጣም ተጨነቀ። እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ “ይህን ከባድ ነገር በእኔ በአገልጋይህ ላይ ስለምን አመጣህብኝ? ለምንስ በፊትህ ሞገስን አላገኘሁም? የዚህን ሁሉ ሕዝብስ ከባድ ኀላፊነት ለምን በእኔ ላይ ጫንከው? ጡት የሚጠባውን ሕፃን አንዲት ሞግዚት እንደምትታቀፈው እኔም እነርሱን ታቅፌ አንተ ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳደርሳቸው የምታደርገኝ እነዚህን ሰዎች እኔ ፀነስኳቸውን? ወይስ እኔ ወለድኳቸውን? የምንበላውን ሥጋ ስጠን እያሉ ወደ እኔ መጥተው ስለሚያለቅሱ ለእነዚህ ሰዎች ሁሉ የሚሆን ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? እኔ ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን መምራት አልችልም፤ ይህ ኀላፊነት ለእኔ እጅግ ከባድ ነው፤ በዚህ ሁኔታ እንድሠቃይ ከምታደርገኝ ይልቅ መከራ እንዳላይ ብትራራልኝና አሁኑኑ ብትገድለኝ ይሻላል።”
ዘኍል 11:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቡም ስለ ደረሰባቸው መከራ በጌታ ላይ አጉረመረሙ፤ ጌታም ሰምቶ እጅግ ተቈጣ፤ የጌታም እሳት በመካከላቸው ነደደ፥ የሰፈሩንም ዳር በላ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ ጌታ ጸለየ፥ እሳቱም ጠፋ። የጌታም እሳት በመካከላቸው ስለ ነደደ የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው። በእነርሱም መካከል የነበረው የተለያየ ሕዝብ እጅግ ጐመጀ፤ የእስራኤልም ልጆች ዳግመኛ ዘወር በለው አለቀሱ እንዲህም አሉ፦ “የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብጽ ሳለን እንዲያው በነጻ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ ሐብሐብውንም፥ ባሕሮውንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስታውሳለን፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀ፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም የሚያው ነገር የለም።” መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር። ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በሸክላም ድስት ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ። ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በእርሱ ላይ ይወርድ ነበር። ሙሴም ሕዝቡ በየወገኑ፥ ሰው ሁሉ በየድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የጌታም ቁጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም በጣም ቅር ተሰኘ። ሙሴም ጌታን እንዲህ አለው፦ “ለምን በባርያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር እንዳደርሳቸው፦ ‘ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንደምታቅፈው እንዲሁ በብብትህ እቀፋቸው’ የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? እነርሱንስ ወልጃቸዋለሁን? እነርሱም በፊቴ እያለቀሱ እንዲህ ይላሉና፦ ‘የምንበላውን ሥጋ ስጠን’፤ እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት አገኛለሁ? ለእኔ እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።”