ነህምያ 5:1-16
ነህምያ 5:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። “ከወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ጋር ብዙዎች ነን፤ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት” የሚሉ ነበሩ። “ከራብ የተነሣም እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንንና ወይናችንን፥ ቤታችንንም አስይዘናል” የሚሉ ነበሩ። ሌሎቹም “ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤ አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፤ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፤ ታላላቆችም እርሻችንንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም” የሚሉ ነበሩ። እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ዐዘንሁ። በልቤም አሰብሁ፤ ታላላቆቹንና ሹሞቹንም፥ “ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ” ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። እኔም፥ “ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን?” አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፤ መልስም አላገኙም። ደግሞም አልሁ፥ “የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? እኔ ደግሞ፥ ወንድሞችም፥ ብላቴኖችም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፤ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። እርሻቸውን፥ የወይናቸውንና የወይራቸውን ቦታ፥ ቤታቸውንም፥ ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።” እነርሱም፥ “እንመልስላቸዋለን፤ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፥ “ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁ የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፥ “አሜን” አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ። ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርተሰስታ ከሃያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞች ለአለቃ የሚገባውን ቀለብ አልበላንም። ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፤ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሰለጥኑ ነበር። እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። ደግሞም የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፤ እርሻም አልገዛሁም፤ ብላቴኖችም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ።
ነህምያ 5:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ወንዶቹና ሚስቶቻቸው አይሁድ ወንድሞቻቸውን በመቃወም ብርቱ ጩኸት አሰሙ፤ አንዳንዶቹ፣ “እኛም ሆነ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን በቍጥር ብዙ ነን፤ ታዲያ ለመብላትም ሆነ በሕይወት ለመቈየት እህል ማግኘት አለብን” አሉ። ሌሎቹ፣ “በራቡ ወቅት እህል ለማግኘት ስንል ዕርሻችንን፣ የወይን ተክል ቦታችንንና ቤታችንን እስከ ማስያዝ ደርሰናል” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “የዕርሻችንንና የወይን ተክል ቦታችንን ግብር ለንጉሡ ለመክፈል ገንዘብ እስከ መበደር ደርሰናል። ምንም እንኳ ከአገራችን ሰዎች ጋራ በሥጋና በደም አንድ ብንሆንም፣ እንደ እነርሱ ልጆች ሁሉ የእኛም ወንዶች ልጆች ጥሩዎች ቢሆኑም፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን ባሮች እንዲሆኑ ሰጥተናል፤ አንዳንድ ሴቶች ልጆቻችን አሁንም በባርነት ላይ ናቸው፤ ዕርሻችንና የወይን ተክል ቦታችን የሌሎች በመሆናቸው እኛ ደካሞች ሆነናል።” እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን አቤቱታዎች በሰማሁ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጣሁ፤ ከዚያም ነገሩን በሐሳቤ ካወጣሁ ካወረድሁ በኋላ፣ መኳንንቱንና ሹማምቱን ገሠጽኋቸው፤ “ከገዛ አገራችሁ ሰዎች ላይ እንዴት ዐራጣ ትበላላችሁ” አልኋቸውም። ስለዚህ ከእነርሱ ጋራ ለመነጋገር ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ፤ “ለአሕዛብ ተሽጠው የነበሩትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን ሁሉ ተቤዥተናቸዋል፤ አሁንም እናንተ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ፤ ይህም መልሰን እንድንቤዣቸው ለማድረግ ብቻ ነው!” አልኋቸው፤ እነርሱም የሚመልሱት አልነበራቸውምና ዝም አሉ። ስለዚህ በመቀጠል እንዲህ አልሁ፤ “ይህ የምታደርጉት ነገር ትክክል አይደለም፤ የጠላቶቻችንን የአሕዛብን ስድብ ለማስወገድ የአምላካችንን መንገድ በፍርሀት መከተል አይገባችሁምን? እኔ፣ ወንድሞቼና ሰዎቼም እንደዚሁ ለሕዝቡ ገንዘብና እህል አበድረናል፤ ዐራጣው ግን ያብቃ። ዕርሻቸውን፣ የወይንና የወይራ ዘይት ተክል ቦታቸውንና ቤታቸውን በቶሎ መልሱላቸው፤ እንዲሁም የምታስከፍሏቸውን የገንዘቡን፣ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና ዘይት አንድ መቶኛ ዐራጣ መልሱላቸው።” እነርሱም፣ “እንመልሳለን፤ ምንም ዐይነት ትርፍ አንጠይቃቸውም፤ እንዳልኸን እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱን ጠራኋቸው፤ መኳንንቱንና ሹማምቱም የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ አማልኋቸው። እንዲሁም የልብሴን ዘርፍ አራግፌ፣ “ይህን የተስፋ ቃል የማይፈጽመውን ማንኛውንም ሰው አምላክ ቤቱንና ንብረቱን እንደዚህ ያራግፈው፤ እንደዚህ ያለውም ሰው ይርገፍ፤ ባዶም ይሁን” አልሁ። በዚህም ጉባኤው ሁሉ፣ “አሜን” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም የገቡትን ቃል ፈጸሙ። ከዚህም በላይ በይሁዳ ምድር አገረ ገዥ ሆኜ ከተሾምሁበት፣ ከአርጤክስስ ሃያኛ ዓመት ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዘመነ መንግሥቱ ድረስ፣ ለዐሥራ ሁለት ዓመት እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ ለአንድ አገረ ገዥ የተመደበውን ምግብ ተቀብለን አልበላንም። ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞዎቹ አገረ ገዦች ግን ከምግቡና ከወይኑ ሌላ፣ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም በመጫን አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ረዳቶቻቸውም እንዲሁ ይጭኑባቸው ነበር። እኔ ግን እግዚአብሔርን ከመፍራቴ የተነሣ እንዲህ ያለውን አላደረግሁም። ከዚህ ይልቅ ራሴን ለዚህ ቅጥር ሥራ ሰጠሁ። ሰዎቼም ሁሉ ለሥራው እዚያው ይሰበሰቡ ነበር፤ ምንም መሬት አልነበረንም።
ነህምያ 5:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። አያሌዎቹም፦ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው፥ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር። አያሌዎቹም፦ ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር። ሌሎቹም፦ ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፥ አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፥ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፥ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር። እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ። በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም፦ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው፥ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። እኔም፦ ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፥ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም። ደግሞም አልሁ፦ የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፥ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፥ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው። እነርሱም፦ እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም፥ እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፦ ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፥ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፦ አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፥ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ። ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርጤክስስ ከሀያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ አሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልበላንም። ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፥ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፥ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሠለጥኑ ነበር፥ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። ደግሞም አጥብቄ የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፥ እርሻም አልገዛንም፥ ብላቴኖቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ።
ነህምያ 5:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በአንድ ወቅት ወንዶችና ሴቶች ወገኖቻቸው በሆኑ የአይሁድ አለቆቻቸው ላይ ከባድ አቤቱታ አሰሙ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ “ብዙ ቤተሰብ ስላለን ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችለን እህል እንፈልጋለን” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ “ከደረሰብን ብርቱ ራብ ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችል እህል ለማግኘት ስንል እርሻችንን፥ የወይን ተክላችንንና ቤታችንን ሁሉ መያዣ አድርገን እስከ መስጠት ደርሰናል” ይሉ ነበር። ሌሎችም ደግሞ “ስለ እርሻችንና ስለ ወይን ተክላችን መንግሥት የጠየቀንን ግብር ለመክፈል የገንዘብ ብድር ተበድረናል፤ ከአይሁድ ወገኖቻችን ጋር ዘራችን አንድ ነው፤ የእኛ ልጆች ከእነርሱ ልጆች የሚለዩበት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ የገዛ ልጆቻችንን ለባርነት አሳልፈን ለመስጠት ተገደናል፤ እንዲያውም ከሴቶች ልጆቻችን አንዳንዶቹ ባሪያዎች ሆነዋል፤ ነገር ግን እርሻችንና የወይን ተክል ቦታችን ስለ ተወሰዱ ኀይል የሌለን ሆነናል” በማለት አቤቱታ አሰሙ። እኔም አቤቱታቸውን በሰማሁ ጊዜ ተቈጣሁ፤ ላደርገው የሚገባኝንም በልቤ ወስኜ የሕዝቡ መሪዎች የሆኑትን ባለሥልጣኖች “እናንተ እኮ የገዛ ወንድሞቻችሁን በመጨቈን አራጣ ታስከፍላላችሁ!” በማለት በቊጣ ገሠጽኳቸው። ለችግሩም መፍትሔ ለማግኘት ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቤ “ለአሕዛብ ሕዝቦች የተሸጡ አይሁድ ወገኖቻችንን ራሳችን ልንቤዣቸው በማሰብ የሚቻለንን ሁሉ አደረግን፤ እናንተ ደግሞ እነሆ፥ የገዛ ወንድሞቻችሁ የሆኑት አይሁድን ወገኖቻቸው ለሆናችሁት ለእናንተ ባርያዎች አድርገው ራሳቸውን እንዲሸጡላችሁ በማድረግ ላይ ትገኛላችሁ!” ብዬ ገሠጽኳቸው፤ መሪዎቹም የሚመልሱት ቃል አጥተው ዝም አሉ። እኔ ግን ንግግሬን በመቀጠል እንዲህ አልኳቸው፤ “ያደረጋችኹት ነገር ትክክል አይደለም! እግዚአብሔርን መፍራትና ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ ይህን አድርጋችሁ ቢሆን ኖሮ፥ አሕዛብ ጠላቶቻችን ባልተዘባበቱብንም ነበር። ሕዝቡ ከእኔ ገንዘብም ሆነ እህል እንዲበደሩ ፈቅጄላቸዋለሁ፤ የሥራ ባልደረቦቼና የእኔ አገልጋዮች የሆኑት ሁሉ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ ፈቅጃለሁ፤ እንግዲህስ ‘የተበደራችሁትን ዕዳ ክፈሉን’ ብለን መጠየቅ ይቅርብን፤ ገንዘብም ሆነ እህል ወይም ወይንና የወይራ ዘይት ቢሆን ያበደራችሁትን ሁሉ ወለዱን ተዉላቸው፤ እርሻቸውን የወይንና የወይራ ዘይት ተክላቸውንና ቤታቸውን ሁሉ አሁኑኑ መልሱላቸው።” መሪዎቹም “እንዳዘዝከን እናደርጋለን፤ የተወሰደባቸውን ሀብትና ንብረት ሁሉ እንመልስላቸዋለን፤ የተበደሩትንም ዕዳ ክፈሉ ብለን አንጠይቃቸውም” ሲሉ መለሱልኝ። እኔም ካህናቱን ወደ ውስጥ ጠርቼ፥ መሪዎቹ የገቡትን ቃል ይፈጽሙ ዘንድ እንዲያስምሉአቸው አደረግሁ። ለብሼው የነበረውንም ልብስ በማውለቅ አራግፌ “ከእናንተ መካከል ማንም ሰው የገባውን የተስፋ ቃል ቢያፈርስ እግዚአብሔር እንደዚህ ያድርገው፤ ቤት ንብረቱንም ወስዶ ባዶ እጁን ያስቀረው” አልኳቸው። በዚያም የተገኘው ሰው ሁሉ በአንድ ድምፅ “አሜን!” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ መሪዎቹም የገቡትን ቃል ፈጸሙ። አርጤክስስ ንጉሠ ነገሥት ከሆነበት ከኻኛው ዓመት ጀምሮ ሠላሳ ሁለት ዓመት እስከ ሆነው ድረስ እኔ የይሁዳ ገዢ በሆንኩበት የዐሥራ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘመዶቼም ሆኑ ወይም እኔ ራሴ ለአንድ አገረ ገዢ የሚገባውን ምግብ አልበላንም። ከእኔ በፊት የሕዝብ ገዢ ሆኖ የተሾመው ሁሉ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም በመሆን፥ በየቀኑ ለምግብና ለመጠጥ የሚሆን አርባ ብር ያስከፍላቸው ነበር፤ የገዢዎቹም አገልጋዮች እንኳ በሕዝቡ ላይ ሠልጥነውባቸው ይጨቊኑአቸው ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንደዚያ አላደረግሁም። ያለኝን ኀይል ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጽር እንደገና በማሳነጽ ተግባር ላይ አዋልኩት እንጂ ለግሌ ምንም ዐይነት ንብረት አልሰበሰብኩም፤ አገልጋዮቼም ሁሉ በዚህ ሥራ ተባበሩኝ፤
ነህምያ 5:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት በወንድሞቻቸው በአይሁድ ላይ ትልቅ ሆነ። እንዲህ የሚሉ ነበሩ፦ “እኛ፥ ወንዶች ልጆቻችንና ሴቶች ልጆቻችን ብዙ ነን፤ እንድንበላና በሕይወት እንድንኖር እህልን እንውሰድ” እንዲህ የሚሉም ነበሩ፦ “በራቡ ጊዜ እህል እንድንወስድ እርሻችን፥ የወይን ቦታችንንና ቤታችንን አስይዘናል” እንዲህ የሚሉ ደግሞ ነበሩ፦ “ለንጉሡ ግብር ለመክፈል እርሻችንንና የወይን ቦታችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤ አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆ ወንዶች ልጆቻችንና ሴቶች ልጆቻችን ባርያዎች እንዲሆኑ ለማምጣት ተገደናል፥ አንደንድ ሴቶች ልጆቻችን አሁንም ለባርነት ተወስደዋል፤ እርሻችንና የወይን ቦታችን ለሌሎች ስለሆነ ኃይል በእጃችን የለም።” እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን ቃላት በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቆጣሁ። በልቤም አሰብሁና መኳንንቶቹንና ሹማምቱን ተከራከርኋቸው፥ እንዲህም አልኋቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ለወንድማችሁ በአራጣ ታበድራላችሁ”፤ ትልቅ ጉባኤም ሰበሰብሁባቸው። እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “ለአሕዛብ የተሸጡትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን መጠን ተቤዠን፥ እናንተ ደግሞ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ? እነርሱስ ለእኛ ይሸጣሉን? እነርሱም ዝም አሉ፥ የሚመልሱትንም ቃል አጡ። እንዲህም አልኳቸው፦ የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት መሄድ አይገባችሁምን? እኔ፥ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ ገንዘብና እህል አበድረናቸዋል፤ ይህን አራጣ ግን እባካችሁ እንተወው። በብድር የያዛችሁትን እርሻቸውን፥ የወይን ቦታቸውን፥ ወይራቸውን፥ ቤታቸውን፥ ከመቶ አንድ የወሰዳችሁትን ብር፥ እህሉን፥ አዲሱን ወይን ጠጅና ዘይት እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።” እነርሱም፦ “እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንፈልግም፤ አንተ እንዳልኸው እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ ቃል እንደገቡት እንዲያደርጉ አስማልኳቸው። ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፦ “ይህን ቃል የማይፈጽመውን ሰው እግዚአብሔር ከቤቱና ከንብረቱ እንደዚሁ ያራግፈው፤ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፦ “አሜን” አሉና ጌታን አመሰገኑ፤ ሕዝቡ ቃል ኪዳኑ አደረጉ። በይሁዳ ምድር ላይ ገዢ እንድሆን ከተሾምሁበት፥ ከንጉሡ አርታሕሻስት ከሀያኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ የንጉሡን ምግብ አልበላንም። ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞ ገዢዎች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደውባቸው ነበር፥ ምግብ፥ ወይና አርባ ሰቅል ብር ከእነሱ ይወስዱ ነበር፤ አገልጋዮቻቸው ደግሞ ሕዝቡን ይጨቁኑአቸው ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። በተጨማሪም ለዚህ የቅጥር ሥራ እራሴን ሰጠሁ፥ እርሻም አልገዛንም፤ አገልጋዮቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ።