የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 8:14-38

ማርቆስ 8:14-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እንጀራ መያዝም ረሱ፤ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። እርሱም “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እርስ በርሳቸውም “እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው “እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዐይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት፤” አሉት። ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም “ሰባት” አሉት። “ገና አላስተዋላችሁምን?” አላቸው። ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፤ እንዲዳስሰውም ለመኑት። ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፤ በዐይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት “አንዳች ታያለህን?” ብሎ ጠየቀው። አሻቅቦም “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ፤” አለ። ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዐይኑ ላይ ጫነበት፤ አጥርቶም አየ፤ ዳነም፤ ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። ወደ ቤቱም ሰደደውና “ወደ መንደሩ አትግባ፤ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር፤” አለው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ፤ በመንገድም “ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ?” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም “መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ” ብለው ነገሩት። “እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ ነህ፤” ብሎ መለሰለት። ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊናቅ፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። እርሱ ግን ዘወር አለ፤ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና “ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና፤” አለ። ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? በዚህም በዘማዊና በኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።

ማርቆስ 8:14-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺሕ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት። እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው። ከዚያም ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፣ እጁንም በላዩ ጭኖ፣ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፣ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ለማዳን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”

ማርቆስ 8:14-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። እርሱም፦ ተጠንቀቁ፥ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው። እርስ በርሳቸውም፦ እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም፦ አሥራ ሁለት አሉት። ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም፦ ሰባት አሉት። ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው። ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት። ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት፦ አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው። አሻቅቦም፦ ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። ወደ ቤቱም ሰደደውና፦ ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም፦ ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም፦ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለ። ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።

ማርቆስ 8:14-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ በጀልባው ውስጥ ከአንድ እንጀራ በቀር ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠንቀቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ፥ ምናልባት እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም ይህንኑ ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እንጀራ ስለሌለን ነው ብላችሁ ስለምን ታስባላችሁ? ገና ምንም የማታስተውሉና የማይገባችሁ ናችሁን? ልባችሁስ ገና እንደ ደነዘዘ ነውን? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮስ እያላችሁ አትሰሙምን? እንዴትስ ትዝ አይላችሁም? ለመሆኑ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ” አሉት። “እንዲሁም ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት መሶብ ሙሉ” አሉት። እርሱም “ታዲያ፥ ገና አታስተውሉምን?” አላቸው። ወደ ቤተ ሳይዳም በደረሱ ጊዜ ሰዎች አንዱን ዕውር ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እንዲዳስሰውም ለመኑት። እርሱም ማየት የተሳነውን ሰው እጅ ይዞ እየመራ ከመንደር ወደ ውጪ አወጣው፤ በሰውየውም ዐይኖች ላይ ምራቁን እንትፍ ብሎ እጁን ጫነበትና “አንዳች ነገር ታያለህን?” ሲል ጠየቀው። ዐይነ ስውሩም ቀና ብሎ፥ “አዎ ሰዎች ይታዩኛል፤ ግን እንደሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ፤” አለ። እንደገናም ኢየሱስ በሰውየው ዐይኖች ላይ እጁን ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው ትኲር ብሎ አየ፤ ድኖም ሁሉን ነገር አጥርቶ ማየት ጀመረ። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ “ወደ መንደሩ አትግባ፤” ብሎ ወደ ቤቱ እንዲሄድ አሰናበተው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የፊልጶስ ቂሳርያ በሚባለው ክፍለ ሀገር አካባቢ ወዳሉት መንደሮች አመሩ፤ በመንገድም ላይ ሳሉ ኢየሱስ፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም፦ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ ሌሎች ኤልያስ ነው፤ ሌሎችም ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል፤” ሲሉ መለሱለት። “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ “አንተ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም፦ “ስለ እኔ ለማንም እንዳትናገሩ፤” ብሎ አስጠነቀቃቸው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል ማስተማር ጀመረ፤ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።” ይህን ነገር በግልጥ ነገራቸው፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ገለል አድርጎት ይገሥጸው ጀመር። “እንዲህ አትበል” ሲል ተቈጣው። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና ጴጥሮስን፦ “አንተ ሰይጣን ከእኔ ኋላ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብም!” ሲል ገሠጸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል፤ ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል? በዚህ በከሐዲና በኃጢአተኛ ትውልድ ፊት በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ እኔም የሰው ልጅ በአባቴ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር ስመጣ በእርሱ አፍርበታለሁ።”

ማርቆስ 8:14-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለረሱ፥ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፥ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፥ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፥ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን” አላቸው። ከዚያም ወደ ቤተሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፥ እጁንም በላዩ ጭኖ፥ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፥ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፥ “ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ላከው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፈልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፥ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፥ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፥ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፥ እንደሚገደል፥ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፥ “አንተ ሰይጣን፥ ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፥ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ለመሆኑ፥ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፥ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”