ማርቆስ 6:1-32

ማርቆስ 6:1-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና “እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን?” አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ፤ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፤ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤” አለ። “በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል፤” አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው። ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል፤ ስለዚህም ኀይል በእርሱ ይደረጋል፤” አለ። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” አሉ፤ ሌሎችም “ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው፤” አሉ። ሄሮድስ ግን ሰምቶ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን “የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም፤” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር፤ አልቻለችም፤ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን “የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ፤ እሰጥሽማለሁ፤” አላት፤ “የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ፤” ብሎ ማለላት። ወጥታም ለእናትዋ “ምን ልለምነው?” አለች። እርስዋም “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለች። ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ፤” ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፤ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፤ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ፤ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።

ማርቆስ 6:1-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፣ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ? ይህ ዐናጺው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፣ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚያም ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ትርፍ እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ በዚያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፣ “የዚህ ዐይነት ታምር በርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፣ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፣ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፣ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷል!” አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፣ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፣ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሠኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከርሱ ጋራ ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ወዲያውኑም ንጉሡ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፣ የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቈረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፣ “እስኪ ብቻችሁን ከእኔ ጋራ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ።

ማርቆስ 6:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና፦ እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው። ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። ሌሎችም፦ ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም፦ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን፦ የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። ወጥታም ለእናትዋ፦ ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች። ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።

ማርቆስ 6:1-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። በሰንበት ቀን በምኲራብ ማስተማር ጀመረ፤ ብዙ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ይሰሙት ነበር፤ እነርሱም “ይህ ሰው ይህን ሁሉ ነገር ከየት አገኘው? ምን ዐይነት ጥበብ ተሰጥቶታል? እነዚህንስ ተአምራት የሚያደርገው እንዴት ነው?” እያሉ ይደነቁ ነበር። ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፥ “ነቢይ በሌሎች ዘንድ ይከበራል፤ በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹና በቤተ ሰቡ መካከል ግን ይናቃል፤” ሲል መለሰላቸው። በዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር ሌላ ተአምር ማድረግ አልቻለም። ሕዝቡ ሳያምኑ በመቅረታቸው እጅግ ተገረመ፤ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገዳቸው ከበትር በቀር እንጀራም ሆነ ከረጢት፥ ገንዘብም በመቀነታቸው እንዳይዙ አዘዛቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀጠባብ እንኳ አትልበሱ፤ በማናቸውም ስፍራ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትገቡ፥ ያንን ስፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቈዩ፤ ሰዎች በማይቀበሉአችሁና በማይሰሙአችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምስክር ይሆንባቸዋል።” የተላኩትም ከዚያ ወጥተው፥ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አስተማሩ። ብዙ አጋንንትንም አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ዝና በሁሉም ዘንድ ስለ ታወቀ፥ ንጉሡ ሄሮድስ ስለ እርሱ ሰማ። አንዳንድ ሰዎች፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል፤ ስለዚህ ይህ ሁሉ ተአምራት በእርሱ ይደረጋል” ይሉ ነበር። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” ይሉ ነበር፤ የቀሩትም ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት እንደ አንዱ ነው፤” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ግን ይህን ሁሉ ሰምቶ፦ “ይህ እኔ አንገቱን ያስቈረጥኩት ዮሐንስ ነው፤ እነሆ! እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮዲያዳን ስለአገባ ዮሐንስን በእርስዋ ምክንያት አስይዞ በወህኒ ቤት አስሮት ነበር። ዮሐንስም የታሰረው፥ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት ማግባትህ ተገቢ አይደለም!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ሄሮዲያዳ በዚህ ተቀይማ ዮሐንስን ልታስገድለው ትፈልግ ነበር፤ ነገር ግን አልቻለችም። ሄሮድስ በመጀመሪያ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ይጠብቀውም ነበር። ሄሮድስ የዮሐንስን ንግግር በሰማ ቊጥር ይታወክ ነበር፤ ይሁን እንጂ በደስታ ይሰማው ነበር። ሄሮድስ የተወለደበትን ቀን ለማክበር ለመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ ለጦር ሹማምንትና ለአንዳንድ የታወቁ የገሊላ ነዋሪዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ለሄሮዲያዳ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላት፤ ስለዚህም የሄሮዲያዳ ልጅ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገብታ እየጨፈረች ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ተጋባዦች አስደሰተች፤ ንጉሡም ልጅትዋን፦ “የምትፈልጊውን ማንኛውንም ነገር ጠይቂኝ፤ እሰጥሻለሁ” አላት፤ “የመንግሥቴንም እኩሌታ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ!” ሲል ማለላት። እርስዋም ወደ እናትዋ ሄዳ፥ “ምን ልጠይቅ?” አለቻት፤ እናትዋም “ ‘የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ይሰጠኝ፤’ ብለሽ ጠይቂ፤” አለቻት። ልጅትዋም ወዲያውኑ በፍጥነት ወደ ንጉሡ ተመልሳ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በሳሕን ሆኖ አሁን እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፤” ስትል ጠየቀች። ንጉሡ በዚህ ነገር በጣም አዘነ፤ ይሁን እንጂ በተጋባዦች ፊት ስላደረገው መሐላ የጠየቀችውን ሊከለክላት አልፈለገም። ስለዚህ ንጉሡ ወዲያውኑ አንዱን የዘብ ጠባቂ ወታደር የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ ላከው፤ ወታደሩም ወደ ወህኒው ቤት ሄዶ የዮሐንስን ራስ ቈረጠ፤ የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አድርጎ አመጣና ለልጅትዋ ሰጣት፤ ልጅትዋም ለእናትዋ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያት ከተላኩበት ተመልሰው መጥተው በኢየሱስ ፊት ተሰበሰቡ፤ ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። እርሱም “እናንተ ብቻችሁን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሂዱና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ወደ እነርሱ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ስለ ነበሩ ለመመገብ እንኳ ጊዜ ሊኖራቸው ስላልቻለ ነው። ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ፥ ሄዱ።

ማርቆስ 6:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፥ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፥ የያዕቆብና የዮሳ፥ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፥ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹ መካከል በቤተሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፥ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቆዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁና የማይሰማችሁ ከሆነ፥ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፥ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፥ “የዚህ ዓይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎቹም፥ “ኤልያስ ነው” አሉ። አንዳንዶች ደግሞ፥ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር። ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፥ እኔ ራሱን ያስቆረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷአል አለ። ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፥ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። ዮሐንስ ሄሮድስን፥ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያዳምጠው ነበር። በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምንቱ፥ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው፤ ንጉሡም ብላቴናዪቱን፥ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሓላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፥ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፥ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ አዘነ፤ በተጋበዙት እንግዶች ፊት የመሐላ ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ስለዚህ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፥ የዮሐንስን ራስ ቆርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቆረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፥ “እስቲ ብቻችሁን ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ።