የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 6:1-32

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 6:1-32 አማ2000

ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና “እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን?” አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ፤ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፤ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤” አለ። “በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል፤” አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው። ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል፤ ስለዚህም ኀይል በእርሱ ይደረጋል፤” አለ። ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” አሉ፤ ሌሎችም “ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው፤” አሉ። ሄሮድስ ግን ሰምቶ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፤” አለ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን “የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም፤” ይለው ነበርና። ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር፤ አልቻለችም፤ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን “የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ፤ እሰጥሽማለሁ፤” አላት፤ “የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ፤” ብሎ ማለላት። ወጥታም ለእናትዋ “ምን ልለምነው?” አለች። እርስዋም “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለች። ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ፤” ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፤ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፤ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ፤ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች