የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 14:53-72

ማርቆስ 14:53-72 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፤ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፤ ምስክርነታቸው ግን አልተስማማም። ሰዎችም ተነሥተው “እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ፤ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ፤” ሲል ሰማነው፤ ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተስማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ “አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው?” ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ፤ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና “የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና “ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ። እነርሱም ሁሉ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና “ትንቢት ተናገር፤” ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና “አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ፤” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም፤ አላስተውልምም፤” ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው፤” ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን “የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም፤” ብሎ እራሱን ይረግምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስንም ኢየሱስ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:53-72 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፣ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፣ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፣ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን፣ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ አለ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፣ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደ ገና ተናገረች። እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፣ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፣ በርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፣ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:53-72 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። ሰዎችም ተነሥተው፦ እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ፦ አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና፦ የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፦ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ስድቡን ሰማችሁ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ፦ ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና፦ ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና፦ አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት፦ ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን፦ የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። እርሱ ግን፦ ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስንም ኢየሱስ፦ ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:53-72 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም። የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። ኢየሱስም “አዎ፥ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታያላችሁ! እንዲሁም በሰማይ ደመና ተመልሶ ሲመጣ ታያላችሁ” አለ። የካህናት አለቃውም በቊጣ ልብሱን ቀደደና “ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? እነሆ! ይህን የስድብ ቃል በእግዚአብሔር ላይ ሲሰነዝር ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” አለ። ሁሉም በአንድ ቃል፥ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ምራቃቸውን እንትፍ ይሉበት ጀመር፤ ዐይኑንም በጨርቅ ሸፍነው “አንተ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደ መታህ ዕወቅ!” እያሉ በቡጢ ይመቱት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ ከካህናት አለቃው ቤት በታች በግቢው ውስጥ እንዳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንድዋ መጣች፤ እርስዋ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኲር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ፤” አለችው። እርሱ ግን “እኔ አላውቅም፤ አንቺ የምትዪውም አይገባኝም፤” ሲል ካደ። ይህንንም ብሎ ወደ ደጃፉ እንደ ወጣ ዶሮ ጮኸ። ገረዲትዋም ጴጥሮስን አይታ፥ በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው!” ስትል እንደገና ትናገር ጀመር፤ እርሱ ግን እንደገና ካደ። ጥቂት ቈየት ብሎም በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው መሆንህን በእርግጥ አነጋገርህ ያስረዳል፤ ስለዚህ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። ወዲያውኑ ዶሮ ሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለውና ምርር ብሎ አለቀሰ።

ማርቆስ 14:53-72 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፥ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፥ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፥ የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፥ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፥ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፥ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና፥ የቡሩኩ ልጅ፥ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፥ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፥ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?”፤ እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፥ “እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፥ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኩር ብላ ተመለከተችውና፥ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ” አለችው። እርሱ ግን፥ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፥ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደገና ተናገረች። እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፥ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፥ በእርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱ ግን፥ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፥ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።