ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፤ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፤ ምስክርነታቸው ግን አልተስማማም። ሰዎችም ተነሥተው “እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ፤ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ፤” ሲል ሰማነው፤ ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተስማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ “አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው?” ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ፤ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና “የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና “ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ። እነርሱም ሁሉ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና “ትንቢት ተናገር፤” ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና “አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ፤” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቅም፤ አላስተውልምም፤” ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው፤” ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን “የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም፤” ብሎ እራሱን ይረግምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስንም ኢየሱስ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።
የማርቆስ ወንጌል 14 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 14
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 14:53-72
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos