ሚክያስ 4:1-5
ሚክያስ 4:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፥ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ። በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፥ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፥ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም። ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።
ሚክያስ 4:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በመጨረሻው ዘመን፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ፣ ከተራሮች ልቆ ይታያል፤ ከኰረብቶች በላይ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤ በመንገዱ እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።” ሕግ ከጽዮን ይመጣል፤ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም። እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤ በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤ ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም። እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሯልና። አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክታቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።
ሚክያስ 4:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፥ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ። በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፥ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፥ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም። ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።
ሚክያስ 4:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ፥ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤ የብዙ መንግሥታት ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፥ “ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ፥ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤ እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤ እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።” እርሱ በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ በቅርብና በሩቅ ባሉ ታላላቅ መንግሥታት መካከል ያለውን አለመግባባት ያስወግዳል፤ ስለ ሆነም ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውንም ወደ ማጭድ ይለውጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ጦርነት አያነሣም፤ ከዚያ በኋላም የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም። እያንዳንዱ ሰው በተከለው ወይንና በለስ ጥላ ሥር በሰላም ያርፋል። የሚያስፈራውም ነገር አይኖርም፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። አሕዛብ ሁሉ እያንዳንዳቸው ጣዖቶቻቸውን ያመልካሉ፤ እኛ ግን አምላካችንን እግዚአብሔርን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እናመልካለን።
ሚክያስ 4:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ይሆናል፥ በመጨረሻው ዘመን የጌታ ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶች በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። ብዙዎች አሕዛብ መጥተው፦ ኑ ወደ ጌታ ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ እኛም በፍለጋው እንሄዳለን ይላሉ፤ ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የጌታ ቃል ይወጣልና። በብዙዎች ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች መንግሥታት ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውን ወደ ማጭድ ለመለወጥ ይቀጠቅጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም። እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም፤ የሠራዊት ጌታ አፍ ተናግሮአልና። ሕዝብ ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳልና፥ እኛ ግን በጌታ አምላካችን ስም ለዘለዓለም ዓለም እንሄዳለን።