ማቴዎስ 3:1-11
ማቴዎስ 3:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። በነቢዩ በኢሳይያስ “ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” የተባለለት ይህ ነውና። ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፤ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበረ። ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም ‘አብርሃም አባት አለን’ እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቍኦረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። እኔስ “ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤
ማቴዎስ 3:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያን ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። ስብከቱም፣ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚል ነበር። በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረለት እርሱ ነው፤ “በምድረ በዳ፣ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አስተካክሉ’ እያለ የሚጮኽ ድምፅ።” የዮሐንስ ልብስ የግመል ጠጕር ሲሆን፣ ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። ከኢየሩሳሌም፣ ከመላው ይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይጐርፉ፣ ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደሚያጠምቅበት ስፍራ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እናንት የእፉኝት ልጆች! ለመሆኑ ከሚመጣው ቍጣ እንድታመልጡ ማን መከራችሁ? ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ‘አብርሃም አባት አለን’ በማለት ራሳችሁን አታታልሉ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣ ይችላል እላችኋለሁና። እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። “እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን መሸከም የማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበልጥ ኀያል ከእኔ በኋላ ይመጣል። እርሱም በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።
ማቴዎስ 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። በነቢዩ በኢሳይያስ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና። ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ። ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፦ ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቍኦረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤
ማቴዎስ 3:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ በረሓ እየሰበከ መጣ። ሲያስተምርም “እነሆ! የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” ይል ነበር። “ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፥ ጥርጊያውንም አቅኑ!’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ” ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ስለ ዮሐንስ ነበር። የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጒር የተሠራ ነበር፤ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የጣዝማ ማር. ነበር፤ በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከመላው የይሁዳ ምድር፥ ከዮርዳኖስም ዙሪያ ሁሉ፥ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይመጡ ነበር። ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ይጠመቁ ነበር። ነገር ግን፥ ዮሐንስ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ለመጠመቅ ወደ እርሱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእባብ ልጆች! ከሚመጣው ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ? እንግዲያውስ ንስሓ መግባታችሁን የሚያመለክት ሥራ ሥሩ። ‘እኛ የአብርሃም ልጆች ነን’ በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ፤ እግዚአብሔር ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣለት ይችላል እላችኋለሁ። አሁን ግን፥ መጥረቢያ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ፥ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል። እነሆ፥ እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ እርሱ ከእኔ እጅግ ይበልጣል፤ እኔ የእግሩን ጫማ እንኳ ለመሸከም የተገባሁ አይደለሁም።
ማቴዎስ 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። እንዲህም አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ።” በነቢዩ በኢሳይያስ “‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” ተብሎ የተነገረለት ይህ ነውና። የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጉር የተሠራ ነበር፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም፥ ከይሁዳ ሁሉና በዮርዳኖስም ዙሪያ ካሉ አውራጃዎች ሁሉ ሰዎች ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ ይጠመቁ ነበር። ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ጥምቀት ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቁጣ እንድታመልጡ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ በልባችሁ ‘አብርሃም አባት አለን’ ብላችሁ አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት ይችላል እላችኋለሁ። አሁንም ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። “እኔ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን ለመሸከም የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤