በዚያን ጊዜ መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ በረሓ እየሰበከ መጣ። ሲያስተምርም “እነሆ! የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” ይል ነበር። “ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፥ ጥርጊያውንም አቅኑ!’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ” ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ስለ ዮሐንስ ነበር። የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጒር የተሠራ ነበር፤ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የጣዝማ ማር. ነበር፤ በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከመላው የይሁዳ ምድር፥ ከዮርዳኖስም ዙሪያ ሁሉ፥ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይመጡ ነበር። ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ይጠመቁ ነበር። ነገር ግን፥ ዮሐንስ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ለመጠመቅ ወደ እርሱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእባብ ልጆች! ከሚመጣው ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ? እንግዲያውስ ንስሓ መግባታችሁን የሚያመለክት ሥራ ሥሩ። ‘እኛ የአብርሃም ልጆች ነን’ በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ፤ እግዚአብሔር ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣለት ይችላል እላችኋለሁ። አሁን ግን፥ መጥረቢያ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ፥ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል። እነሆ፥ እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ እርሱ ከእኔ እጅግ ይበልጣል፤ እኔ የእግሩን ጫማ እንኳ ለመሸከም የተገባሁ አይደለሁም።
የማቴዎስ ወንጌል 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 3:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos