ማቴዎስ 27:46-60
ማቴዎስ 27:46-60 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አድርጎ አጠጣው። ሌሎቹ ግን “ተው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ፤” አሉ። ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፤” ብለው እጅግ ፈሩ። ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ። በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፤ ከዐለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፤ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።
ማቴዎስ 27:46-60 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸንበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት። የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ። ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ። በዚያ ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ዐብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፣ “ይህስ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ። ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ። ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ። ምሽት ላይ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱ ራሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ። ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ የበፍታ ጨርቅ ከፈነው፤ ለራሱ ከዐለት አስፈልፍሎ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባልሎ የመቃብሩን በር ዘግቶ ሄደ።
ማቴዎስ 27:46-60 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም፦ አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው፦ ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው። ሌሎቹ ግን፦ ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ። ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው፦ ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ። ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ። በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።
ማቴዎስ 27:46-60 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ። ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውንም ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” አሉ። በሩቅ ሆነው የሚመለከቱት ብዙ ሴቶችም በዚያ ነበሩ፤ እነርሱ ከገሊላ ጀምረው ኢየሱስን እያገለገሉ ይከተሉት የነበሩ ናቸው። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙባቸው ነበር። በመሸ ጊዜ ዮሴፍ የሚባል አንድ የአርማትያስ ከተማ ሀብታም ሰው ወደዚያ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ ይህ ሰው፥ ወደ ጲላጦስ ሄደና የኢየሱስን አስከሬን ለመነ፤ ጲላጦስም አስከሬኑ እንዲሰጠው አዘዘ። ስለዚህ ዮሴፍ አስከሬኑን አውርዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው። ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀው በራሱ አዲስ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ከዚህ በኋላ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን በር ዘጋና ሄደ።
ማቴዎስ 27:46-60 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ኢየሱስ “ኤሊ ኤሊ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆሙት ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሰምተው “ኤልያስን ይጠራል” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠና ሰፍነግ ወስዶ የወይን ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አስሮ አጠጣው። የተቀሩት ግን “ተወው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ። እነሆ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው ከነበሩት የብዙ ቅዱሳን በድን ተነሣ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስቷ ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አሉ። ኢየሱስን እያገለገሉት ከገሊላ የተከተሉት፥ በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ ብዙ ሴቶች እዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያምና የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ። በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀመዝሙር ነበረ፤ እርሱም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፤ ከዐለት በወቀረው በአዲሱ መቃብሩ አኖረው፤ በመቃብሩ በር ላይ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።