ማቴዎስ 26:17-35
ማቴዎስ 26:17-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ?” አሉት። እርሱም “ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል’ በሉት፤” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል፤” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ፤” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፤ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣም።” መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ፤’ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ፤” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
ማቴዎስ 26:17-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን ራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ለዚያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው። እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከእንግዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’ ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሌሎች በሙሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም!” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ።
ማቴዎስ 26:17-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። እርሱም፦ ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስ፦ እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ጴጥሮስ፦ ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
ማቴዎስ 26:17-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “የፋሲካ በዓልን ራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “ወደ ከተማው ስትገቡ ወደምታገኙት ሰው ቤት ሂዱና ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በዓል ራት የምበላው በአንተ ቤት ነው ይላል’ በሉት” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የፋሲካውንም ራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። ሲበሉም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አለ። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር በጣም አዝነው፥ እያንዳንዳቸው ጌታ ሆይ፥ “እኔ እሆን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ከእኔ ጋር በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፥ “መምህር ሆይ! እኔ እሆን?” አለ። ኢየሱስም፥ “አንተ እንዳልከው ነው” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና በዚህች ሌሊት፥ ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም!” ብሎ ተናገረ። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” አለው። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንዲሁ ይሉ ነበር።
ማቴዎስ 26:17-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አለ “ወደ ከተማ ወደ አንድ ሰው ሄዳችሁ ‘መምህሩ እንዲህ ይላል፥ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት አደርጋለሁ ይላል’ በሉት።” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካውንም አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው። ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና፥ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደዚሁ አሉ።