ማቴዎስ 25:1-10

ማቴዎስ 25:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“በዚያ ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች። ከእነርሱም ዐምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ ዐምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋራ መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ። “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው። “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው። “ዘይት ሊገዙ እንደ ሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ ዐብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።

ማቴዎስ 25:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው፥ ሙሽራ ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ልጃገረዶች ትመስላለች። ከእነርሱ አምስቱ ሞኞች፥ አምስቱ ብልኆች ነበሩ። ሞኞቹ ልጃገረዶች መብራታቸውን ቢይዙም ለመብራቱ የሚሆን ትርፍ ዘይት አልያዙም ነበር። ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ከመብራታቸው ጋር ትርፍ ዘይት በዕቃ ይዘው ነበር፤ ሙሽራው በመዘግየቱ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ተኙ። “እኩለ ሌሊት ሲሆን ግን ‘እነሆ፥ ሙሽራው መጣ! ውጡና ተቀበሉት!’ የሚል ውካታ ተሰማ። በዚያን ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ልጃገረዶች ብልኆቹን መብራታችን መጥፋቱ ስለ ሆነ እባካችሁ ከዘይታችሁ ስጡን አሏቸው። ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ‘ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንም። ይልቅስ ወደ ሱቅ ሂዱና ለእናንተ የሚሆን ዘይት ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሞኞቹ ልጃገረዶች፥ ዘይት ለመግዛት በሄዱበት ወቅት ሙሽራው መጣ። ተዘጋጅተው የነበሩትም ልጃገረዶች ከሙሽራው ጋር ወደ ሠርጉ ግብዣ አዳራሽ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።