የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 21:18-46

ማቴዎስ 21:18-46 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና “ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ፤” አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው “በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች?” ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ፤” አላቸው። ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው?” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ “ ‘ከሰማይ’ ብንል ‘እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው’ ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ። ለኢየሱስም መልሰው “አናውቅም” አሉት። እርሱም ደግሞ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው። “ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ ‘ልጄ ሆይ! ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ፤’ አለው። እርሱም መልሶ ‘አልወድም፤’ አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ ‘እሺ ጌታዬ፤’ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?” “ፊተኛው” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፤ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም። “ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጥመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤ ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፤ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን ‘ልጄንስ ያፍሩታል፤’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ፤’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል፤” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።” የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።

ማቴዎስ 21:18-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤ በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በስተቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከእንግዲህ ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷ ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ግባ’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤ እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀርበው፣ “ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ መልሱን ብትነግሩኝ፣ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት የመጣው ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?” እነርሱም እርስ በርስ በመነጋገር እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው?’ ካልን ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች ነው’ ካልን ደግሞ፣ ‘ሕዝቡ ዮሐንስን ነቢይ ነው’ ብሎ ስለሚያምን እንፈራለን።” ስለዚህ፣ “አናውቅም” ብለው ለኢየሱስ መለሱለት። እርሱም፣ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ምን ይመስላችኋል? ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበረ፤ ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ፣ ‘ልጄ ሆይ፤ ዛሬ ወደ ወይኑ ቦታ ሄደህ ሥራ’ አለው። “ልጁም፣ ‘አልሄድም’ አለው፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ። “ወደ ሁለተኛው ልጁ ሄዶ እንደዚያው አለው፤ ልጁም ‘እሺ ጌታዬ እሄዳለሁ’ አለው፤ ነገር ግን ሳይሄድ ቀረ። “ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም፣ “የመጀመሪያው ልጅ” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል፤ መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። የሆነውን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም። “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የወይን ዕርሻ ባለቤት ነበረ፤ በዕርሻው ዙሪያ ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። “ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም፣ ‘ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ። “ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን? አላቸው፤ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማእዘን ራስ ሆነ፤ እግዚአብሔር ይህን አድርጓል፤ ሥራውም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።” የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።

ማቴዎስ 21:18-46 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና፦ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው፦ በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው። ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና፦ በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፦ ከሰማይ ብንል፦ እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ለኢየሱስም መልሰው፦ አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ፦ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ፦ አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም። ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን፦ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? እነርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።

ማቴዎስ 21:18-46 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ጠዋት በማለዳ፥ ወደ ከተማ ተመልሶ ሲሄድ ራበው፤ አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ይህች የበለስ ዛፍ በአንድ አፍታ እንዴት ደረቀች!” በማለት ተገረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ በበለሲቱ ዛፍ ላይ እንደ ተደረገው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህንን ተራራ እንኳ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር!’ ብትሉት ይሆንላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ያስተምር ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀረቡና “ይህን ሁሉ የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ ለጥያቄዬ መልስ ከሰጣችሁኝ እኔም ይህን ሁሉ በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከየት መጣ? ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው?” እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት፥ ሕዝቡን እንፈራለን።” ስለዚህ “አናውቅም” ሲሉ ለኢየሱስ መለሱለት። እርሱም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን ሁሉ እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ታዲያ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ከእነርሱ ወደ አንደኛው ቀርቦ፥ ‘ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ወደ ወይን አትክልት ቦታዬ ሄደህ እንድትሠራ ይሁን’ አለው። ልጁም ‘እምቢ አልሄድም’ አለ። ይሁን እንጂ በኋላ ተጸጸተና ሊሠራ ሄደ። አባትየው ወደ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ ሄደና እርሱንም እንዲሁ እንዲሠራ አዘዘው፤ ልጁም ‘እሺ አባቴ እሄዳለሁ’ አለ። ነገር ግን አልሄደም። እንግዲህ ከነዚህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው ነዋ!” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ወደ መንግሥተ ሰማይ በመግባት ይቀድሙአችኋል። መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ቢመጣ አላመናችሁትም፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ ይህንንም አይታችሁ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ በወይኑ አትክልት ዙሪያ አጥር ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ረዥም ግንብ ሠራ፤ ከዚህ በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የፍሬ ወራት በደረሰ ጊዜ ድርሻውን እንዲቀበሉለት አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። የወይኑ አትክልት ባለቤት እንደገና ቊጥራቸው ከፊተኞቹ የሚበልጥ ሌሎችን አገልጋዮች ደግሞ ላከ። ገበሬዎቹ በእነርሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም የወይኑ አትክልት ጌታ ‘ልጄንስ ያከብሩታል!’ በማለት ልጁን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እኛ እንውረስ!’ ተባባሉ። ልጁንም ይዘው ከወይን አትክልቱ ቦታ ውጪ ወሰዱና ገደሉት። “ታዲያ፥ የወይኑ አትክልት ባለቤት በመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “የእነዚህን ክፉ ሰዎች ፍጻሜ የከፋ ያደርገዋል። የወይኑንም ተክል ቦታ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “በቅዱሳት መጻሕፍት ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ ዋና የማእዘን ራስ ሆነ፤ ይህም የጌታ ሥራ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ ተብሎ የተጻፈውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬ ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። [ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።”] የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን እነዚህን ምሳሌዎች በሰሙ ጊዜ ኢየሱስ የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ተገነዘቡ። ስለዚህ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያየው ስለ ነበር ፈሩ።

ማቴዎስ 21:18-46 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ራበው። በመንገድ ዳር የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን ከቅጠል በስተቀር ምንም አላገኘባትም፤ “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስዋ ዛፍም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህንን አይተው በመደነቅ “የበለስዋ ዛፍ ወዲያውኑ እንዴት ደረቀች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ፥ በበለሲቱ ዛፍ እንደተደረገው ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ወደ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እኔም ደግሞ አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?” እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተነጋገሩ “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች’ ነው ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ። ለኢየሱስም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ መጀመሪያውም ሄዶ ‘ልጄ ሆይ! ዛሬ ወደ ወይኔ አትክልት ሥፍራ ሂድና ሥራ’ አለው። እርሱም ‘አልሄድም’ አለ፤ ቆይቶ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ሄዶ እንዲሁ አለው እርሱም ‘እሺ ጌታዬ’ ብሎ መለሰለት፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ዘማውያን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ ወደ እናንተ መጥቶ ነበር፥ አላመናችሁትም፤ ቀራጮችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ በመጨረሻም ይህንን አይታችሁ እንኳ ልታምኑት ንስሐ አልገባችሁም። “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ የእርሻ ባለቤት ነበረ፤ እርሱም ቅጥር ቀጠረለት፤ መጭመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራለት፤ እርሻውንም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበት ወራት በደረሰ ጊዜ፥ ፍሬውን እንዲቀበሉለት ባርያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹም ባርያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበዙ ሌሎች ባርያዎችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጉባቸው። በመጨረሻም ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት ሥፍራ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ሥፍራ ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ሁኔታ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ሥፍራ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሕፍት አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ያደቅቀዋል።” ሊቃነ ካህናትና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አወቁ። ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ፈሩ።