ኢየሱስ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤ በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በስተቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከእንግዲህ ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷ ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነቅለህ ባሕር ውስጥ ግባ’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤ እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀርበው፣ “ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ መልሱን ብትነግሩኝ፣ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት የመጣው ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?” እነርሱም እርስ በርስ በመነጋገር እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው?’ ካልን ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች ነው’ ካልን ደግሞ፣ ‘ሕዝቡ ዮሐንስን ነቢይ ነው’ ብሎ ስለሚያምን እንፈራለን።” ስለዚህ፣ “አናውቅም” ብለው ለኢየሱስ መለሱለት። እርሱም፣ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ምን ይመስላችኋል? ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበረ፤ ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ፣ ‘ልጄ ሆይ፤ ዛሬ ወደ ወይኑ ቦታ ሄደህ ሥራ’ አለው። “ልጁም፣ ‘አልሄድም’ አለው፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ። “ወደ ሁለተኛው ልጁ ሄዶ እንደዚያው አለው፤ ልጁም ‘እሺ ጌታዬ እሄዳለሁ’ አለው፤ ነገር ግን ሳይሄድ ቀረ። “ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም፣ “የመጀመሪያው ልጅ” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል፤ መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። የሆነውን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም። “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የወይን ዕርሻ ባለቤት ነበረ፤ በዕርሻው ዙሪያ ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። “ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም፣ ‘ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ። “ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን? አላቸው፤ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማእዘን ራስ ሆነ፤ እግዚአብሔር ይህን አድርጓል፤ ሥራውም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።” የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።
ማቴዎስ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 21
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 21:18-46
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos