ማቴዎስ 20:1-19

ማቴዎስ 20:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“መንግሥተ ሰማይ በወይኑ አትክልት ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ጠዋት በማለዳ የወጣውን የአትክልት ባለቤት ትመስላለች። እርሱ ለእያንዳንዱ በቀን አንድ ዲናር ሊከፍል ተዋውሎ፥ ሠራተኞችን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ ላካቸው። በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ፥ ሥራ ፈተው በአደባባይ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አየ፤ ‘እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዳችሁ ሥሩ፤ የሚገባችሁንም ሒሳብ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። እነርሱም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዱ፤ ደግሞም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎች ሰዎች ቆመው አገኘና ‘እናንተስ ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ‘የሚቀጥረን ሰው አጥተን ነው’ አሉት፤ እርሱም ‘እንግዲያውስ፥ እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሂዱና ሥሩ’ አላቸው። “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሥራ ኀላፊውን ‘ሠራተኞቹን ጥራና በመጨረሻ ከተቀጠሩት ጀምረህ በፊት እስከ ተቀጠሩት ድረስ የሥራ ዋጋቸውን ክፈላቸው’ አለው። ስለዚህ በዐሥራ አንድ ሰዓት የተቀጠሩት ቀርበው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በፊት የተቀጠሩት በቀረቡ ጊዜ ይበልጥ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ገንዘቡን ተቀበሉና በወይኑ አትክልት ባለቤት ላይ እንዲህ እያሉ አጒረመረሙ፤ ‘እነዚህ በመጨረሻ መጥተው የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ሙቀት እየተቃጠልን በሥራ ስንደክም ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው።’ የወይኑ አትክልት ባለቤትም ከሠራተኞቹ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ወዳጄ ሆይ! ምንም አልበደልኩህም፤ የተዋዋልነው በቀን አንድ ዲናር ልከፍልህ አይደለምን? ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያኽል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈቀድኩ። በገዛ ገንዘቤ የፈለግኹትን ማድረግ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ ለጋሥ ስለ ሆንኩ አንተ ትመቀኛለህ?’ ” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “እንዲሁም ኋለኞች የሆኑ ፊተኞች ፊተኞች የሆኑትም ኋለኞች ይሆናሉ፤” አለ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር፤ በመንገድም ሳሉ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወደ እርሱ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ አሁን ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ በዚያም የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል። ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያላግጡበታል፤ ይገርፉታል፤ ይሰቅሉታልም፤ ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።”

ማቴዎስ 20:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና። ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው። በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፤ እነዚያንም ‘እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ፤’ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና ‘ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤’ አሉት። እርሱም ‘እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ፤’ አላቸው። በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን ‘ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ተቀብለውም ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው፤’ ብለው በባለቤቱ ላይ አንጕኦራጕኦሩ። እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዐይንህ ምቀኛ ናትን? እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።’ ” ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አላቸው።

ማቴዎስ 20:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“መንግሥተ ሰማይ ለወይኑ ቦታ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ የወጣን የአትክልት ስፍራ ባለቤት ትመስላለች። በቀን አንዳንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከተስማሙ በኋላ ሠራተኞቹን በወይኑ ቦታ አሰማራቸው። “ከጧቱ ሦስት ሰዓት ላይ በመውጣት ሥራ ፈትተው በገበያ ቦታ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አግኝቶ፣ ‘እናንተም ሄዳችሁ በወይኔ ቦታ ሥሩ፤ ተገቢውን ክፍያ እሰጣችኋለሁ’ አላቸው፤ እነርሱም ሄዱ። “ከቀኑ በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ላይ ወጥቶ ሌሎች የቀን ሠራተኞችን ቀጠረ። ከሰዓት በኋላም በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና፣ ‘ቀኑን ሙሉ ያለ ሥራ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ በማለት ጠየቃቸው። “እነርሱም፣ ‘የሚቀጥረን ሰው ስለ ዐጣን ነው’ አሉት። “እርሱም፣ ‘እናንተም ሄዳችሁ በወይኔ ቦታ ሥሩ’ አላቸው። “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሠራተኞቹን ተቈጣጣሪ፣ ‘ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ያሉትን ሠራተኞች በሙሉ ጥራና ደመወዛቸውን ክፈላቸው’ አለው። “በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ገደማ የተቀጠሩት ሠራተኞች ቀርበው፣ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ዲናር ተቀበሉ። በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲቀርቡ ብልጫ ያለው ክፍያ የሚያገኙ መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አንዳንድ ዲናር ተከፈላቸው። ክፍያውን ሲቀበሉ በባለቤቱ ላይ በማጕረምረም፣ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክምና በፀሓይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋራ እንዴት እኩል ትከፍለናለህ?’ አሉት። “እርሱም አንደኛውን ሠራተኛ እንዲህ አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ በደል አላደረስሁብህም፤ በአንድ ዲናር ለመሥራት ከእኔ ጋራ ተስማምተህ አልነበረምን? በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ። ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኛነት ያዘህን?’ “ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።” ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ እንዲያላግጡበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል።”

ማቴዎስ 20:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና። ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው። በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፥ እነዚያንም፦ እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና፦ ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ? አላቸው። የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው አሉት። እርሱም፦ እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ አላቸው። በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን፦ ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው። በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ተቀብለውም፦ እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፥ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው ብለው በባለቤቱ ላይ አንጕኦራጕኦሩ። እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን? እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና። ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ፦ እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።

ማቴዎስ 20:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“መንግሥተ ሰማይ በወይኑ አትክልት ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ጠዋት በማለዳ የወጣውን የአትክልት ባለቤት ትመስላለች። እርሱ ለእያንዳንዱ በቀን አንድ ዲናር ሊከፍል ተዋውሎ፥ ሠራተኞችን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ ላካቸው። በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ፥ ሥራ ፈተው በአደባባይ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አየ፤ ‘እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዳችሁ ሥሩ፤ የሚገባችሁንም ሒሳብ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። እነርሱም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዱ፤ ደግሞም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎች ሰዎች ቆመው አገኘና ‘እናንተስ ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ‘የሚቀጥረን ሰው አጥተን ነው’ አሉት፤ እርሱም ‘እንግዲያውስ፥ እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሂዱና ሥሩ’ አላቸው። “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሥራ ኀላፊውን ‘ሠራተኞቹን ጥራና በመጨረሻ ከተቀጠሩት ጀምረህ በፊት እስከ ተቀጠሩት ድረስ የሥራ ዋጋቸውን ክፈላቸው’ አለው። ስለዚህ በዐሥራ አንድ ሰዓት የተቀጠሩት ቀርበው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በፊት የተቀጠሩት በቀረቡ ጊዜ ይበልጥ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ገንዘቡን ተቀበሉና በወይኑ አትክልት ባለቤት ላይ እንዲህ እያሉ አጒረመረሙ፤ ‘እነዚህ በመጨረሻ መጥተው የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ሙቀት እየተቃጠልን በሥራ ስንደክም ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው።’ የወይኑ አትክልት ባለቤትም ከሠራተኞቹ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ወዳጄ ሆይ! ምንም አልበደልኩህም፤ የተዋዋልነው በቀን አንድ ዲናር ልከፍልህ አይደለምን? ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያኽል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈቀድኩ። በገዛ ገንዘቤ የፈለግኹትን ማድረግ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ ለጋሥ ስለ ሆንኩ አንተ ትመቀኛለህ?’ ” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “እንዲሁም ኋለኞች የሆኑ ፊተኞች ፊተኞች የሆኑትም ኋለኞች ይሆናሉ፤” አለ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር፤ በመንገድም ሳሉ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወደ እርሱ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ አሁን ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ በዚያም የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል። ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያላግጡበታል፤ ይገርፉታል፤ ይሰቅሉታልም፤ ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።”

ማቴዎስ 20:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ የአትክልት ቦታ ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ትመስላለችና። ከሠራተኞቹ ጋር በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሰደዳቸው። ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አየ፤ እነርሱንም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ፤’ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። ወደ ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። እነርሱም ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤’ አሉት። እርሱም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤’ አላቸው። በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ ሹሙን ‘ሠራተኞቹን ጥራና ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የገቡት መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። መጀመሪያ የመጡትም በቀረቡ ጊዜ የበለጠ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በተቀበሉም ጊዜ በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። እንዲህም አሉት ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑን ድካምና ሐሩር ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው።’ እርሱ ግን ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም፤ ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን? የአንተ የሆነውን ውሰድና ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁህን ያህል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈለግሁ። የራሴ በሆነ ነገር ላይ የወደድሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንኩ ትመቀኛለህን? ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።’” ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ሳለ፥ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወሰዳቸው፥ በመንገድም ሳሉ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄድን ነው፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ እንዲያላግጡበት፥ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።”