“መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ የአትክልት ቦታ ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ትመስላለችና። ከሠራተኞቹ ጋር በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሰደዳቸው። ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አየ፤ እነርሱንም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ፤’ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። ወደ ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። እነርሱም ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤’ አሉት። እርሱም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤’ አላቸው። በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ ሹሙን ‘ሠራተኞቹን ጥራና ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የገቡት መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። መጀመሪያ የመጡትም በቀረቡ ጊዜ የበለጠ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በተቀበሉም ጊዜ በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። እንዲህም አሉት ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑን ድካምና ሐሩር ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው።’ እርሱ ግን ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም፤ ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን? የአንተ የሆነውን ውሰድና ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁህን ያህል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈለግሁ። የራሴ በሆነ ነገር ላይ የወደድሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንኩ ትመቀኛለህን? ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።’” ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ሳለ፥ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወሰዳቸው፥ በመንገድም ሳሉ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄድን ነው፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ እንዲያላግጡበት፥ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።”
የማቴዎስ ወንጌል 20 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 20:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች