ማቴዎስ 18:1-9

ማቴዎስ 18:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?” አሉት። ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ፤ እንዲህም አለ “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። “እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር። “ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፤ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሀል። ዐይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዐይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

ማቴዎስ 18:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ አንድ ሕፃን ወደ ራሱ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመና እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ካልተለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ፣ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው። ማንም እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል። “ነገር ግን ማንም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል፣ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥሎ ቢሰጥም ይሻለዋል። ይህች ዓለም የመሰናክል ምክንያት በመሆኗ ወዮላት! መሰናክል መምጣቱ አይቀርምና፤ ነገር ግን የመሰናክሉ ምክንያት ለሚሆነው ሰው ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል፣ ዐንካሳ ወይም ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። እንዲሁም ዐይንህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

ማቴዎስ 18:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት። ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ እንዲህም አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር። ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት። እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቍኦርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ህይወት መግባት ይሻልሀል። ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

ማቴዎስ 18:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም አንድ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ፤ እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፦ ካልተለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል። “ማንም ሰው በእኔ ከሚያምኑት ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያስት ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢጣልና ቢሰጥም ይሻለዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሰዎች እንዲሰናከሉ በሚያደርጉት ነገሮች ምክንያት ለዓለም ወዮላት! መቼም የሚያሰናክሉ ነገሮች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን የመሰናከያው መምጫ ለሚሆነው ለዚያ ሰው ወዮለት! ስለዚህ እጅህ ወይም እግርህ ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው! ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል ይልቅ ጒንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዐይንህም ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ አውጥተህ ወዲያ ጣለው! ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

ማቴዎስ 18:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያች ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ሕፃን ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው፤ እንዲህም አለ “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንደዚህ ሕፃን ትሑት የሆነ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጠው እርሱ ነው። “እንደዚህ ሕፃን ያለውን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል። “ከማሰናከያው የተነሣ ዓለም ወዮላት፤ ማሰናከያ ግድ ይመጣልና፤ የማሰናከያ ማምጫ ምክንያት የሆነው ያ ሰው ግን ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ካሰናከለህ ቆርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል፥ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህ ካሰናከለህ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፥ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል።