የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 18:1-9

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 18:1-9 አማ2000

በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?” አሉት። ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ፤ እንዲህም አለ “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። “እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር። “ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፤ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሀል። ዐይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዐይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች