የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 17:14-21

ማቴዎስ 17:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤ ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” ኢየሱስም፣ “አንት የማታምን ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤ እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ። ልጁን ወደዚህ አምጡት” አለ። ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸውና ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነ። ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤ የዚህ ዐይነቱ ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በስተቀር አይወጣም።”

ማቴዎስ 17:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ሕዝቡ በተመለሱ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ በእግሩ ሥር ተንበረከከና እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! እባክህ ለልጄ ራራለት፤ የሚጥል የጋኔን በሽታ ክፉኛ ያሠቃየዋል፤ በእሳት ላይና በውሃ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይወድቃል። ወደ ደቀ መዛሙርትህም አምጥቼው ነበር፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” ኢየሱስም “እናንተ የማታምኑ ጠማማ ትውልድ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “እኛ ጋኔኑን ለማውጣት ያልቻልነው ስለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እምነታችሁ ጐደሎ ስለ ሆነ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወዲያ ሂድ!’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ምንም ነገር አይኖርም። እንዲህ ዐይነቱ ጋኔን ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር ከቶ አይወጣም።”