የማቴዎስ ወንጌል 17
17
የኢየሱስ መልክ መለወጥ
(ማር. 9፥2-13፤ ሉቃ. 9፥28-36)
1ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ፥ ለብቻው ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ። #2ጴጥ. 1፥17-18። 2እዚያ በፊታቸው መልኩ ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። 3እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። 4በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው።
5ጴጥሮስ ገና ይህን ሲናገር ሳለ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። #ዘፍ. 22፥2፤ ዘዳ. 18፥15፤ መዝ. 2፥7፤ ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ 12፥8፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22።
6ደቀ መዛሙርቱም ይህን ድምፅ በሰሙ ጊዜ እጅግ ስለ ደነገጡ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። 7ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ቀርቦ በእጁ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፤ አትፍሩ!” አላቸው። 8እነርሱም ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም።
9ከተራራው ሲወርዱ ሳሉ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።
10ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ፥ የሕግ መምህራን አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። #ሚል. 4፥5።
11ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ እርሱ ሁሉንም ያስተካክላል። 12ነገር ግን ኤልያስ ገና ዱሮ መጥቶአል እላችኋለሁ፤ ሰዎች ግን አላወቁትም፤ ስለዚህ የፈለጉትን ሁሉ አደረጉበት። እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ በእነርሱ እጅ መከራን መቀበል አለበት።” #ማቴ. 11፥14።
13በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የተናገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑ ገባቸው።
ኢየሱስ ጋኔን ያደረበትን ልጅ መፈወሱ
(ማር. 9፥14-29፤ ሉቃ. 9፥37-43)
14ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ሕዝቡ በተመለሱ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ በእግሩ ሥር ተንበረከከና እንዲህ አለ፦ 15“ጌታ ሆይ! እባክህ ለልጄ ራራለት፤ የሚጥል የጋኔን በሽታ ክፉኛ ያሠቃየዋል፤ በእሳት ላይና በውሃ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይወድቃል። 16ወደ ደቀ መዛሙርትህም አምጥቼው ነበር፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” 17ኢየሱስም “እናንተ የማታምኑ ጠማማ ትውልድ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። 18ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ።
19ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “እኛ ጋኔኑን ለማውጣት ያልቻልነው ስለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 20ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እምነታችሁ ጐደሎ ስለ ሆነ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወዲያ ሂድ!’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ምንም ነገር አይኖርም። #ማቴ. 21፥21፤ ማር. 11፥23፤ 1ቆሮ. 13፥2። 21እንዲህ ዐይነቱ ጋኔን ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር ከቶ አይወጣም።” #17፥21 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቁ. 21 ይጨምራሉ፤ ቃሉም በማር. 9፥29 ያለውን ይመስላል።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ከሞት ስለ መነሣቱ ሁለተኛ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማር. 9፥30-32፤ ሉቃ. 9፥43-45)
22ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ 23እነርሱ ይገድሉታል፤ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር እጅግ አዘኑ።
የቤተ መቅደስ ግብር ስለ መክፈል
24ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም በደረሱ ጊዜ የቤተ መቅደስ ግብር ተቀባዮች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና፥ “መምህራችሁ የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” ሲሉ ጠየቁት። #ዘፀ. 30፥13፤ 38፥26። 25ጴጥሮስም “ኧረ ይከፍላል” አላቸው። ጴጥሮስ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ “ስምዖን ጴጥሮስ ሆይ! ምን ይመስልሃል? የዚህ ዓለም መንግሥታት ቀረጥና ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ነውን ወይስ ከውጪ አገር ሰዎች?” ሲል ጠየቀው። 26ጴጥሮስም “ከውጪ አገር ሰዎች ነው” ሲል መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲያውስ ልጆቻቸው ግብር ከመክፈል ነጻ ናቸው ማለት ነዋ? 27ነገር ግን ለእነርሱ እንቅፋት እንዳንሆንባቸው ወደ ባሕር ሂድና መንጠቆ ጣል፤ በመጀመሪያ የሚወጣውን ዓሣ ያዝ፤ አፉንም ስትከፍት በውስጡ ገንዘብ ታገኛለህ፤ ያንንም ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ክፈል።”
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997