የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 17:1-9

ማቴዎስ 17:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ፤” አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆም፥ ከደመናው “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፤ አትፍሩም፤” አላቸው። ዐይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ፤” ብሎ አዘዛቸው።

ማቴዎስ 17:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ረዥም ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ። በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ በዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው። እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው። ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም። ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው።

ማቴዎስ 17:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና፦ ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ፦ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው።

ማቴዎስ 17:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ፥ ለብቻው ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ። እዚያ በፊታቸው መልኩ ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው። ጴጥሮስ ገና ይህን ሲናገር ሳለ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ድምፅ በሰሙ ጊዜ እጅግ ስለ ደነገጡ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ቀርቦ በእጁ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፤ አትፍሩ!” አላቸው። እነርሱም ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራው ሲወርዱ ሳሉ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።

ማቴዎስ 17:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ደግሞ ለኤልያስ የሚሆን ሦስት ዳሶችን በዚህ እንሥራ” አለው። እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆ ከደመናው ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የተወደደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀመዛሙርቱ ይህንን ሰምተው በፊታቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም መጥቶ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፥ አትፍሩ” አላቸው። ዐይኖቻቸውን በገለጡ ጊዜ ግን ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ብሎ አዘዛቸው።