ማቴዎስ 17:1-21
ማቴዎስ 17:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ፤” አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆም፥ ከደመናው “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፤ አትፍሩም፤” አላቸው። ዐይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ፤” ብሎ አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም “እንግዲህ ጻፎች ‘ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል፤’ ስለ ምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ “ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ። ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ! ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበትክፉኛ ይሣቀያልና፤ ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውሃ ይወድቃልና። ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው፤” አለው። ኢየሱስም መልሶ “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት፤” አለ። ኢየሱስም ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፤ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና “እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው?” አሉት። ኢየሱስም “ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ወደዚያ እለፍ፤’ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ይህ ዐይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም፤” አላቸው።
ማቴዎስ 17:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ረዥም ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ። በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ በዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው። እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው። ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም። ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ታዲያ የኦሪት ሕግ መምህራን፣ ኤልያስ አስቀድሞ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ መጥቶ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስ መጥቷል፤ ሆኖም የፈለጉትን ነገር አደረጉበት እንጂ አላወቁትም። እንዲሁም የሰው ልጅ በእጃቸው መከራን ይቀበላል።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ተረዱ። ወደ ሕዝቡ እንደ ተመለሱ፣ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ልጄን ማርልኝ፤ በሚጥል በሽታ እጅግ እየተሠቃየ ነው፤ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥ ይወድቃል፤ ውሃ ውስጥም ይገባል፤ ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” ኢየሱስም፣ “አንት የማታምን ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤ እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ። ልጁን ወደዚህ አምጡት” አለ። ከዚያም ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸውና ከልጁ ወጣ፤ ልጁም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነ። ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛ ጋኔኑን ማስወጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤ የዚህ ዐይነቱ ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በስተቀር አይወጣም።”
ማቴዎስ 17:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና፦ ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ፦ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም፦ እንግዲህ ጻፎች፦ ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ፦ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ። ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ፦ ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና፤ ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና። ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። ኢየሱስም ገሠጸው ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፥ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት። ኢየሱስም፦ ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ፦ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።
ማቴዎስ 17:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ፥ ለብቻው ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ። እዚያ በፊታቸው መልኩ ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው። ጴጥሮስ ገና ይህን ሲናገር ሳለ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ድምፅ በሰሙ ጊዜ እጅግ ስለ ደነገጡ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ቀርቦ በእጁ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፤ አትፍሩ!” አላቸው። እነርሱም ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራው ሲወርዱ ሳሉ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ፥ የሕግ መምህራን አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ እርሱ ሁሉንም ያስተካክላል። ነገር ግን ኤልያስ ገና ዱሮ መጥቶአል እላችኋለሁ፤ ሰዎች ግን አላወቁትም፤ ስለዚህ የፈለጉትን ሁሉ አደረጉበት። እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ በእነርሱ እጅ መከራን መቀበል አለበት።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የተናገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑ ገባቸው። ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ሕዝቡ በተመለሱ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ በእግሩ ሥር ተንበረከከና እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! እባክህ ለልጄ ራራለት፤ የሚጥል የጋኔን በሽታ ክፉኛ ያሠቃየዋል፤ በእሳት ላይና በውሃ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይወድቃል። ወደ ደቀ መዛሙርትህም አምጥቼው ነበር፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” ኢየሱስም “እናንተ የማታምኑ ጠማማ ትውልድ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “እኛ ጋኔኑን ለማውጣት ያልቻልነው ስለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እምነታችሁ ጐደሎ ስለ ሆነ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወዲያ ሂድ!’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ምንም ነገር አይኖርም። እንዲህ ዐይነቱ ጋኔን ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር ከቶ አይወጣም።”
ማቴዎስ 17:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ደግሞ ለኤልያስ የሚሆን ሦስት ዳሶችን በዚህ እንሥራ” አለው። እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆ ከደመናው ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የተወደደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ደቀመዛሙርቱ ይህንን ሰምተው በፊታቸው ወደቁ፤ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም መጥቶ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፥ አትፍሩ” አላቸው። ዐይኖቻቸውን በገለጡ ጊዜ ግን ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራው እየወረዱ ሳሉ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ብሎ አዘዛቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ ጻፎች ‘ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል’ ለምን ይላሉ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ኤልያስ በእርግጥ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ነገር ግን ኤልያስ ከዚህ በፊት መጥቷል እላችኋለሁ፤ ነገር ግን የፈለጉትን ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበላል” አላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አወቁ። ወደ ሕዝቡም በመጡ ጊዜ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ! ልጄን ማርልኝ፥ በሚጥል በሽታ ክፉኛ ይሣቀያል፤ ብዙ ጊዜ በእሳት ላይ ብዙ ጊዜ ደግሞ በውሃ ውስጥ ይወድቃልና። ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የማያምንና ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት” ኢየሱስም ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፤ ልጁም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” አሉት። እርሱም የእምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ “ከዚህ ወደዚያ ሂድ” ብትሉት ይሄዳል፤ የሚያቅታችሁ ምንም ነገርም የለም። እንዲህ ዓይነቱ በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር ከቶ አይወጣም።