የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 16:1-12

ማቴዎስ 16:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሊፈትኑት በመሻት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ምሽት ላይ፣ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ ንጋት ላይም፣ ‘ሰማዩ ቀልቷል፣ ከብዷልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚያም ኢየሱስ ትቷቸው ሄደ። ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። ኢየሱስም፣ “ልብ በሉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱ ግን እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ እንጀራ ስለ አለመያዛችሁ ለምን ትነጋገራላችሁ? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።

ማቴዎስ 16:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው “በመሸ ጊዜ ‘ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ። ማለዳም ‘ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፤ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን? ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።” ትቶአቸውም ሄደ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ፤” አላቸው። እነርሱም “እንጀራ ባንይዝ ነው፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም?” እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።

ማቴዎስ 16:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በመሸ ጊዜ፦ ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤ ማለዳም፦ ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን? ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። እነርሱም፦ እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ እምነት የጕኦደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።

ማቴዎስ 16:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው “ከሰማይ ተአምር አሳየን” ሲሉ ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ [“በማታ ሰማይ ቀልቶ ስታዩ ‘ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ ሲነጋ በጠዋት ደግሞ ‘ሰማዩ ደመና ሆኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል’ ትላላችሁ፤ የሰማዩንስ መልክ መለየት ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም።] ክፉና የማያምን ትውልድ፥ ምልክት ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ትቶአቸው ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ማዶ በተሻገሩ ጊዜ ረስተው እንጀራ አልያዙም ነበር፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ልብ አድርጉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” አላቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ ምናልባት እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” በማለት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ‘እንጀራ ስላልያዝን ነው’ ብላችሁ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና የማታስተውሉ ናችሁን? አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባት እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንግዲህ ‘ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ!’ ብዬ ስነግራችሁ ስለ እንጀራ አለመሆኑን እንዴት አታስተውሉም?” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ተጠንቀቁ ያላቸው ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዳልሆነ ተገነዘቡ።

ማቴዎስ 16:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሊፈትኑት መጡና ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ሲመሽ ‘ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ። ጠዋት ደግሞ ‘ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ መለየት ታውቃላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መለየት አትችሉም። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።” ከዚህ በኋላ ትቶአቸው ሄደ። ደቀመዛሙርቱ ወደ ማዶ በሚሻገሩበት ጊዜ እንጀራ መያዝን ረስተው ነበር። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ብለው አሰቡ። ኢየሱስም ይህንን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስላልያዛችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? አሁንም አታስተውሉምን? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ በቅቶ ስንት መሶብ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ በቅቶ ስንት ቅርጫት እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ።” ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠነቀቁ እንዳልነገራቸው ተገነዘቡ።