ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሊፈትኑት በመሻት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ምሽት ላይ፣ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ ንጋት ላይም፣ ‘ሰማዩ ቀልቷል፣ ከብዷልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚያም ኢየሱስ ትቷቸው ሄደ። ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። ኢየሱስም፣ “ልብ በሉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱ ግን እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ እንጀራ ስለ አለመያዛችሁ ለምን ትነጋገራላችሁ? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።
ማቴዎስ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 16:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos