ሉቃስ 6:1-11
ሉቃስ 6:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቈርጠው በእጃቸው እያሹ በሉ። ፈሪሳውያንም፥ “በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩትም በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንደ ገባ፥ ከካህናቱም ብቻ በቀር ሊበሉት የማይገባውን የመሥዋዕቱን ኅብስት ወስዶ እንደ በላ፥ አብረውት ለነበሩትም እንደ ሰጣቸው አላነበባችሁምን? የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው። ከዚህም በኋላ በሌላይቱ ሰንበት ወደ ምኵራቡ ገባና አስተማራቸው፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ። ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከሱበት ምክንያት ያገኙ ዘንድ፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ብለው ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን ዐሳባቸውን ያውቅባቸው ነበርና እጁ የሰለለችውን ሰው፥ “ተነሥተህ በመካከል ቁም” አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት ሊደረግ የሚገባው ምንድነው? መልካም መሥራት ነውን? ወይስ ክፉ መሥራት? ነፍስን ማዳን ነውን? ወይስ መግደል?” እነርሱም ዝም አሉ፤ ወደ እነርሱም ዙሮ ከተመለከተ በኋላ፦ ያን ሰው፥ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውዬውም ዘረጋት፤ እጁም ዳነችና እንደ ሁለተኛይቱ ሆነች። እነርሱ ግን፥ እጅግ ተቈጡ፤ በጌታችን በኢየሱስም ምን እንድሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተማከሩ።
ሉቃስ 6:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው። በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከስሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካከል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። ሰዎቹ ግን በቍጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ።
ሉቃስ 6:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ፦ በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው። ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ፦ ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም። በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው፦ ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ።
ሉቃስ 6:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ በእጃቸው ማሸትና መብላት ጀመሩ፤ ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርቱን “በሰንበት ቀን ሊደረግ የማይገባውን ነገር ስለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እርሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ የመባ ኅብስት አንሥቶ በላ፤ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው፤” አላቸው። በሌላም ሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ እዚያም ቀኝ እጁ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ወንጀል ለማግኘት ፈልገው፥ “እስቲ በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ እንይ፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እጀ ሽባውን “ተነሥና በመካከል ቁም!” አለው፤ ሽባውም ተነሣና በመካከል ቆመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ ለመሆኑ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነውን? ወይስ ክፉ? ነፍስን ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ኢየሱስ በዙሪያው ወዳሉት ሰዎች ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እጀ ሽባውን፥ “እጅህን ዘርጋ!” አለው። እርሱም እጁን በዘረጋው ጊዜ ዳነለትና እንደ ሌላው እጅ ደኅና ሆነ። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ግን በጣም ተቈጥተው በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተመካከሩ።
ሉቃስ 6:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ስለምን ታደርጋላችሁ?” ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ እንዲህ አለ፦ “ዳዊት በተራበ ጊዜ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን ነገር አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር ለመብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን ኅብስት ወስዶ እንዴት እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንዴት እንደሰጣቸው ይገልጥ የለምን?” እርሱም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤” አላቸው። እነሆ በሌላ ሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከስሱበትን ምክንያት ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፦ “ተነሣና በመካከል ቁም፤” አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነውን ወይንስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ነውን ወይንስ ማጥፋት?” በዙርያው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ከቃኘ በኋላ ሰውዬውን፦ “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። እርሱም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ደኅና ሆነ። እነርሱ ግን በቁጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስም ላይ ምን እንደሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።