የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 6:1-11

የሉቃስ ወንጌል 6:1-11 መቅካእኤ

እነሆ፥ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ስለምን ታደርጋላችሁ?” ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ እንዲህ አለ፦ “ዳዊት በተራበ ጊዜ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን ነገር አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር ለመብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን ኅብስት ወስዶ እንዴት እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንዴት እንደሰጣቸው ይገልጥ የለምን?” እርሱም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤” አላቸው። እነሆ በሌላ ሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም የሚከስሱበትን ምክንያት ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፦ “ተነሣና በመካከል ቁም፤” አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነውን ወይንስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ነውን ወይንስ ማጥፋት?” በዙርያው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ከቃኘ በኋላ ሰውዬውን፦ “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። እርሱም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ደኅና ሆነ። እነርሱ ግን በቁጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስም ላይ ምን እንደሚያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።