ሉቃስ 24:33-49
ሉቃስ 24:33-49 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርትና አብረዋቸው የነበሩትንም ተሰብስበው አገኙአቸው፤ እንዲህ እያሉ፥ “ጌታችን በእውነት ተነሥቶአል፤ ለስምዖንም ታይቶታል።” እነርሱም በመንገድ የሆነውንና እንጀራውን ሲቈርስ ጌታችንን እንዴት እንዳወቁት ነገሩአቸው። ይህንም ሲነጋገሩ ጌታችን ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አትፍሩ፤ እኔ ነኝ” አላቸው። እነርሱ ግን ፈሩ፤ ደነገጡም፤ ምትሐትንም የሚያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ምን ያስደነግጣችኋል? በልባችሁስ እንዲህ ያለ ዐሳብ ለምን ይነሣሣል? እጄንና እግሬን እዩ፤ ዳስሱኝም፤ እኔ እንደ ሆንሁም ዕወቁ፤ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና።” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። ከድንጋጤ የተነሣም ገና ሳያምኑ ደስ ብሎአቸውም ሲያደንቁ ሳሉ፥ “በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፤ ከማር ወለላም ጥቂት ሰጡት። ተቀብሎም በፊታቸው በላ፤ የተረፈውንም አንሥቶ ሰጣቸው። እርሱም፥ “በሙሴ ኦሪት፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ እንዳለው፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የነገርኋችሁ ነገሬ ይህ ነው” አላቸው። ከዚህም በኋላ መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው፥ “ክርስቶስ እንዲሞት በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንዲነሣ፥ ንስሓና የኀጢኣት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንዲሰበክ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ነገር ምስክሮች ናችሁ። እነሆ፥ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ።”
ሉቃስ 24:33-49 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በርግጥ ተነሥቷል! ለስምዖንም ታይቷል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቍራሽ ሰጡት፤ እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
ሉቃስ 24:33-49 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም፦ ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው። ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም፦ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፦ በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ። እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።
ሉቃስ 24:33-49 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነርሱም በዚያችው ሰዓት ተነሡና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ፤ በዚያም ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርት አብረዋቸው ካሉት ጋር በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል!” ይሉ ነበር። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው በመንገድ ላይ የሆነውን ነገርና ጌታ ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁትም ተረኩላቸው። እነርሱም ይህን ሲናገሩ ሳሉ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱ ግን መንፈስ የሚያዩ መስሎአቸው ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትደነግጣላችሁ፤ ስለምንስ በልባችሁ ትጠራጠራላችሁ? እጆቼንና እግሮቼን አይታችሁ እኔ ራሴ መሆኔን ዕወቁ፤ ዳሳችሁም እዩኝ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም።” ይህንንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው፤ እነርሱም ከደስታና ከአድናቆት ብዛት የተነሣ ገና አላመኑም ነበር። ኢየሱስም “አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት። እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። ኢየሱስም፥ “ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ የነገርኳችሁ ቃል ይህ ነው” አላቸው። ከዚህ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተዋል እንዲችሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው፤ “መሲሕ መከራ እንደሚቀበልና በሦስተኛው ቀን ከሞት እንደሚነሣ አስቀድሞ ተጽፎአል፤ እንዲሁም በስሙ የንስሓና የኃጢአት ይቅርታ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በየአገሩ ለሕዝብ ሁሉ እንደሚሰበክ ተነግሮአል። እናንተም የዚህ ሁሉ ነገር ምስክሮች ናችሁ፤ እነሆ! እኔ አባቴ የሰጣችሁን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተም ከላይ ኀይል እንደ ልብስ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።”
ሉቃስ 24:33-49 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትንም በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ በእርግጥ ተነሥቷል፥ ለስምዖንም ታይቷል” ይሉ ነበር። እነርሱም በመንገድ የሆነውን፥ እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህንንም ሲነጋገሩ ሳለ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው “ስለምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ያድራል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ ዳስሱኝና እዩ፥ መንፈስ በእኔ እንደምታዩት፥ ሥጋና አጥንት የለውምና፤” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ ብዛት ገና ሳያምኑ ገና በመገረም ላይ ሳሉ “በዚህ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ። ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው “እንዲህ ተጽፏል፥ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንደሚሰበክ፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በዚህች ከተማ ቆዩ።”