ሉቃስ 23:26-29
ሉቃስ 23:26-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በወሰዱትም ጊዜ የቀሬና ሰው ስምዖንን ከዱር ሲመለስ ያዙት፤ ከጌታችን ከኢየሱስም በስተኋላ መስቀሉን አሸከሙት። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና።
ሉቃስ 23:26-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት። ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና።
ሉቃስ 23:26-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት። ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ።
ሉቃስ 23:26-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ኢየሱስን ወሰዱት፤ ይዘውት ሲሄዱ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ እርሱን ይዘው የኢየሱስን መስቀል አሸከሙትና ኢየሱስን እንዲከተል አደረጉት። ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ።
ሉቃስ 23:26-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው ያዙትና መስቀሉን ጭነውበት ከኢየሱስ በኋላ እንዲሄድ አደረጉት። ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና።