ሉቃስ 22:7-20
ሉቃስ 22:7-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የፋሲካን በግ የሚያርዱባት የቂጣ በዓልም ደረሰች። ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን፥ “ሂዱና የምንበላውን የፋሲካ በግ አዘጋጁልን” አላቸው። እነርሱም፥ “ወዴት ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ?” አሉት። እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ከተማ በገባችሁ ጊዜ፥ የውኃ ማድጋ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደሚገባበትም ቤት እርሱን ተከተሉት። የዚያን ቤት ጌታ፦ መምህር ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በግ የምበላበት ቤት ወዴት ነው? ብሎሃል በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” በሄዱም ጊዜ እንዳላቸው አገኙ፤ የፋሲካውንም በግ አዘጋጁ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በማዕድ ተቀመጠ፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ተቀመጡ። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ከመከራዬ አስቀድሞ ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ ወደድሁ። ነገር ግን፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ እንግዲህ ከእርሱ እንደማልበላ እነግራችኋለሁ” አላቸው። ጽዋውንም ተቀብሎ አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህን እንኩ ሁላችሁም ተካፈሉት። እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ፤ እንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” ኅብስቱንም አነሣ፤ አመስገነ፤ ፈትቶም ሰጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “ስለ እናንተ ቤዛ ሆኖ የሚሰጥ ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤” እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋዉን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።
ሉቃስ 22:7-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤ ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።” እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤ እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት የዚህ ትርጕም እስኪፈጸም ድረስ ይህን ፋሲካ ዳግመኛ አልበላም።” ጽዋውን ተቀብሎ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ “ዕንካችሁ፤ ሁላችሁ ከዚህ ተካፈሉ፤ እላችኋለሁና፤ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከምትመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ አልጠጣም።” እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው።
ሉቃስ 22:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም፦ ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። እነርሱም፦ ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። እርሱም አላቸው፦ እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም፦ ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና፦ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።
ሉቃስ 22:7-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስ “የፋሲካውን ራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ሲል ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም “የፋሲካውን ራት የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማ ስትገቡ እነሆ፥ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ። የቤቱንም ጌታ መምህራችን፥ ‘ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሄደው፥ ሁሉ ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በዚያ አዘጋጁ። የእራት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን የፋሲካ ራት ለመብላት እጅግ እመኝ ነበር፤ የዚህ ነገር እውነተኛ ምሥጢር በእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን የፋሲካ ራት ከቶ አልበላም እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንካችሁ ይህንን ተካፈሉ፤ በእውነት እላችኋለሁ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ከወይን ፍሬ የሚገኘውን መጠጥ አልጠጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ፤ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፤ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሰጣቸው። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው።
ሉቃስ 22:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የፋሲካም በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም “ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን፤” ብሎ ላካቸው። እነርሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም አላቸው “እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል የት ነው?’ ይልሃል በሉት፤ እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈውን ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።” ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም “ከመከራዬ በፊት ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም እላችኋለሁና፤” አላቸው። ጽዋንም ተቀበሎ፥ አመስግኖም “እንካችሁ፤ ይህን በመካከላችሁ ተካፈሉት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም እላችኋለሁና” አለ። ኅብስትንም አንሥቶ፥ አመስግኖ፥ ቆረሰና እንዲህ ሲል ሰጣቸው፦ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት”። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።