ሉቃስ 22:47-53
ሉቃስ 22:47-53 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳም ይመራቸው ነበር፤ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸውም ምልክት ይህ ነበር፤ “የምስመው እርሱ ነውና እርሱን አጽንታችሁ ያዙት” አላቸው። ጌታችን ኢየሱስም ይሁዳን፥ “በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?” አለው። አብረውት የነበሩትም የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ጌታችን ኢየሱስን፥ “አቤቱ፥ በሰይፍ ልንመታቸው ትፈቅዳለህን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው፤ ቀኝ ጆሮውንም ቈረጠው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህንስ ተው” አለ፤ ወዲያውም ጆሮውን ዳስሶ አዳነው። ጌታችን ኢየሱስም ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፥ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፥ “ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? ዘወትርም ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስ ስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፤ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው።”
ሉቃስ 22:47-53 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳስሶ ፈወሰው። ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።”
ሉቃስ 22:47-53 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን፦ ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን መልሶ፦ ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም፦ ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው።
ሉቃስ 22:47-53 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብዙ ሰዎች መጡ፤ መሪያቸው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት የነገሩን ሁኔታ ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። ከእነርሱም አንዱ የካህናት አለቃውን አገልጋይ በሰይፍ መታና ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ። ኢየሱስ ግን “ተው! እንደዚህ ያለ ነገር ደግመህ አታድርግ!” አለ፤ የሰውዬውንም ጆሮ ዳስሶ አዳነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፥ የቤተ መቅደስ የዘብ አዛዦችንና የሕዝብ ሽማግሌዎችንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን እንደ ወንበዴ ልትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ስገኝ አልያዛችሁኝም ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ ጊዜና የጨለማው ሥልጣን ጊዜ ነው።”
ሉቃስ 22:47-53 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህንን እየተናገረ እያለ፥ እነሆ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፦ “ይህንስ ተው” አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለቤተ መቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር በመቅደስ ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ሆኖም ይህ የእናንተ ጊዜና ጨለማው የሚሰፍንበት ወቅት ነው፤” አላቸው።