ሉቃስ 22:27-50
ሉቃስ 22:27-50 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሚበልጥ ማንኛው ነው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው ነው? ወይስ የሚላላከው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው አይደለምን? እነሆ፥ እኔ በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። ነገር ግን ስለ እኔ የታገሣችሁ እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ናችሁ። አባቴ ለእኔ እንደ ሰጠኝ፥ እኔም ለእናንተ መንግሥትን አዘጋጅላችኋለሁ፤ በመንግሥቴ በማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በወንበሮችም ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዱ ዘንድ።” ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ፥ “ስምዖን፥ ስምዖን ሆይ፥ ሰይጣን እንደ አጃ ሊያበጥራችሁ አሁን ልመናን ለመነ። እኔ ግን ሃይማኖታችሁ እንዳይደክም ስለ እናንተ ጸለይሁ፤ አንተም ተመልሰህ ወንድሞችህን አጽናቸው።” እርሱም፥ “አቤቱ፥ እኔ ለመታሰርም ቢሆን፥ ለሞትም ቢሆን እንኳ ከአንተ ጋራ ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ” አለው። እርሱ ግን፥ “ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ እንደማታውቀኝ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ደግሞም፥ “ያለ ስልቻ፥ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ በውኑ የተቸገራችሁት ነገር ነበርን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የለም” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “አሁን ግን ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ ያድርግ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁ፥ ከኃጥኣን ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ይደርሳል፤ ስለ እኔ የተጻፈውም ሁሉ ይፈጸማል።” እነርሱም፥ “አቤቱ፥ እነሆ፥ እዚህ በእኛ ዘንድ ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያስ ይበቃችኋል” አላቸው። ወጥቶም እንዳስለመደው ይጸልይ ዘንድ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ከዚያም ደርሶ፥ “ወደ መከራ እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። የድንጋይ ውርወራ ያህልም ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ እየሰገደ ጸለየ። እንዲህም አለ፥ “አባት ሆይ፥ ብትፈቅድስ ይህን ጽዋ ከእኔ አሳልፈው፤ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው። ፈራ፤ መላልሶም ጸለየ፤ ላቡም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆነ። ከሚጸልይበትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ፤ ከኀዘንም የተነሣ ተኝተው አገኛቸው። “ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ” አላቸው። ይህንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳም ይመራቸው ነበር፤ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸውም ምልክት ይህ ነበር፤ “የምስመው እርሱ ነውና እርሱን አጽንታችሁ ያዙት” አላቸው። ጌታችን ኢየሱስም ይሁዳን፥ “በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?” አለው። አብረውት የነበሩትም የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ጌታችን ኢየሱስን፥ “አቤቱ፥ በሰይፍ ልንመታቸው ትፈቅዳለህን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው፤ ቀኝ ጆሮውንም ቈረጠው።
ሉቃስ 22:27-50 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው። እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋር ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ። እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሷል።” ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት። እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው። ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስስ ነበር። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣ “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው። እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።
ሉቃስ 22:27-50 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ። ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ። እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም፦ ይበቃል አላቸው። ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ፦ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም፦ አባት ሆይ፥ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው፦ ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው። ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን፦ ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።
ሉቃስ 22:27-50 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማእድ ተቀምጦ ከሚመገበውና ቆሞ ከሚያገለግለው የትኛው ነው ትልቅ? ትልቅ የሚባለው በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። እናንተ በመከራዬ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቈይታችኋል። ስለዚህ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም እናንተን እሾማችኋለሁ። በመንግሥቴም በማእድ ተቀምጣችሁ ትበላላችሁ፤ ትጠጣላችሁ፤ በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ስምዖን! ስምዖን! እነሆ፥ ገበሬ ስንዴውን ከገለባ አበጥሮ እንደሚለይ እንዲሁም ሰይጣን እናንተን ሊያበጥራችሁ ፈለገ። ነገር ግን የአንተ እምነት እንዳይጠፋ እኔ ለአንተ እጸልያለሁ፤ እንደገና በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ለእስራትም ሆነ ለሞት ከአንተ ጋር አብሬ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ!” አለ። ኢየሱስ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ‘አላውቀውም’ ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የገንዘብ ቦርሳ፥ ከረጢት፥ ጫማም ሳትይዙ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የጐደለብን ነገር አልነበረም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሳም ሆነ ከረጢት ያለው ይያዝ፤ ሰይፍም የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ስለ እኔ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ስለሚገባው ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በእኔ ላይ መፈጸም አለበት እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ!” አሉት። እርሱም “ይበቃል!” አላቸው። ኢየሱስ ከከተማ ወጥቶ እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41 ከዚህ በኋላ የድንጋይ ውርወራ ያኽል ከእነርሱ ራቅ ብሎ ሄደ፤ ተንበርክኮም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ! ፈቃድህ ቢሆን ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” በዚያን ጊዜ የሚያበረታታው መልአክ ከሰማይ መጥቶ ታየው። ልቡም በጣም ተጨንቆ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ከጸሎቱ ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ ከሐዘን ብዛት የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትተኛላችሁ? ይልቅስ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብዙ ሰዎች መጡ፤ መሪያቸው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት የነገሩን ሁኔታ ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። ከእነርሱም አንዱ የካህናት አለቃውን አገልጋይ በሰይፍ መታና ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ።
ሉቃስ 22:27-50 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለመሆኑ ማነው ታላቅ? በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በእናንተ መሀል እንደሚያገለግል ነኝ። እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ ለመንግሥት እሾማችኋላሁ፤ በመንግሥቴም ከእኔ ማዕድ ትበላላአችሁ፥ እንዲሁም ትጠጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይም ለመፍረድ በዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁ። ጌታም “ስምዖን ስምዖን ሆይ! እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና፤” አለ። እርሱም “ጌታ ሆይ! ወደ ወኅኒም ሆነ ወደ ሞት ከአንተ ጋር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ፤” አለው። እርሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፥ ‘አላውቅህም’ እያልህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚያም፥ “ያለ ቦርሳና ያለ ከረጢት፥ ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም” አሉ። እርሱም “አሁን ግን ቦርሳ ያለው ይያዘው፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። ይህ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ የግድ መፈጸም አለበት እላችኋልለሁ፤ አዎን፤ ስለ እኔ የተባለው አሁን ይፈጸማልና፤” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ፤” አሉት። እርሱም “ይበቃል፤” አላቸው። እንደ ለመደው ወጥቶም ወደ ደብረዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ፤” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፤ ተንበርክኮም፦ “አባት ሆይ! ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ፤” እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም የሚያበረታው መልአክ ታየው። በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ፤” አላቸው። ይህንን እየተናገረ እያለ፥ እነሆ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።