ሉቃስ 2:7-20
ሉቃስ 2:7-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የበኵር ልጅዋንም ወለደች፤ አውራ ጣቱንም አሰረችው፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በበረትም አስተኛችው፤ በማደርያቸው ቦታ አልነበራቸውምና። በዚያ ሀገር እረኞች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሀትንም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው። ለእናንተም ምልክቱ እንዲህ ነው፦ ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፥ በጨርቅም ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኛላቸሁ።” ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። “ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፥ ሰላምም በምድር፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” ይሉ ነበር። ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በዐረጉ ጊዜ እነዚያ እረኞች ሰዎች እርስ በርሳቸው፥ “እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ” አሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፤ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝቶ አገኙት። በአዩም ጊዜ የነገሩአቸው ስለዚህ ሕፃን እንደ ሆነ ዐውቀው አወሩ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ የነገሩአቸውን አደነቁ። ማርያም ግን ይህን ሁሉ ትጠብቀው፥ በልብዋም ታኖረው ነበር። እረኞችም እንደ ነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።
ሉቃስ 2:7-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው። በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወድዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። ይህንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።
ሉቃስ 2:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።
ሉቃስ 2:7-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያም የበኲር ልጅዋን ወለደች፤ በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ አስተኛችው። በዚያም አካባቢ፥ በሜዳ ላይ ሌሊት መንጋቸውን እየጠበቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። እነሆ፥ ለእነርሱ የጌታ መልአክ ታያቸው፤ የጌታም የክብር ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ እነርሱም በጣም ፈሩ፤ መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ! ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እነሆ! ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ምልክቱም ይህ ነው፤ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በበረት ውስጥ በግርግም ላይ ተኝቶ ታገኛላችሁ።” በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመልአኩ ጋር አብረው ታዩ፤ እግዚአብሔርንም በማመስገን፥ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!” ይሉ ነበር። መላእክቱ ተለይተዋቸው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ ወደ ቤተልሔም እንሂድ፤ አሁን የተፈጸመውንና ጌታ የገለጠልንን ነገር እንይ” ተባባሉ። በፍጥነት ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑንም በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ ተኝቶ አዩት። ሕፃኑንም ካዩ በኋላ መልአኩ ስለ እርሱ የነገራቸውን አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ ባወሩላቸው ነገር ተደነቁ። ማርያም ግን፥ ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ ይዛ ታሰላስለው ነበር። እረኞቹ፥ ሁሉ ነገር መልአኩ እንዳላቸው ሆኖ በማየታቸውና በመስማታቸው፥ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ፥ ወደ ስፍራቸው ተመለሱ።
ሉቃስ 2:7-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም አካባቢ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!” አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ፤ ጌታም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፤” ተባባሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ቃል ገለጡ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰላሰለች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም ተነግሯቸው እደነበረው ሁሉን ስለ ሰሙና ስለ አዩ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።