ሉቃስ 2:21-48
ሉቃስ 2:21-48 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስምንት ቀን በተፈጸመ ጊዜም ሕፃኑን ሊገዝሩት ወሰዱት፤ በማኅፀንዋ ሳትፀንሰው መልአኩ እንዳወጣለትም ስሙን ኢየሱስ አሉት። የመንጻታቸውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ እንደ ሙሴ ሕግ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሙት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። “በኵር ሆኖ የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይባላል” ተብሎ በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ታዘዘ ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ስለ እርሱ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡለት ዘንድ። በኢየሩሳሌምም ስሙ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ጻድቅና ደግ ሰው ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን ደስታቸውን ያይ ዘንድ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ነበር። የእግዚአብሔርንም መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። መንፈስም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደው፤ ዘመዶቹም በሕግ የተጻፈውን ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ጌታችን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ በአገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ በክንዱ ታቀፈው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው። እንዲህም አለ፤ “አቤቱ፥ እንደ አዘዝህ ዛሬ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ። ዐይኖች ትድግናህን አይተዋልና። በወገንህ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፥ ለአሕዛብ ብርሃንን፥ ለወገንህ ለእስራኤልም ክብርን ትገልጥ ዘንድ።” ዮሴፍና እናቱ ግን በእርሱ ላይ ስለሚናገረው ያደንቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው፤ ባንቺ ግን በልብሽ ፍላጻ ይገባል፤ የብዙዎቹን ዐሳብ ይገልጥ ዘንድ።” ከአሴር ወገን የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል ነቢይት ነበረች፤ አርጅታም ነበር፤ ከድንግልናዋም በኋላ ከባል ጋር ሰባት ዓመት ኖረች። ሰማንያ አራት ዓመትም መበለት ሆና ኖረች፤ በጾምና በጸሎትም እያገለገለች፥ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አትወጣም ነበር። ያንጊዜም ተነሥታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ድኅነት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለ እርሱ ተናገረች። በእግዚአብሔርም ሕግ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ጥበብንም የተመላ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረች። ዘመዶቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንደ አስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ። ሥራቸውንም ጨርሰው ተመለሱ፤ ሕፃኑ ጌታችን ኢየሱስ ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ ዮሴፍና እናቱም አላወቁም ነበር። በመንገድም ከሰዎች ጋር ያለ መስሎአቸው ነበር፤ ያንድ ቀን መንገድንም ከሄዱ በኋላ ዕለቱን ከዘመዶቹ፥ ከሚያውቁትም ዘንድ ፈለጉት። ባላገኙትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ቀን በቤተ መቅደስ በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት። የሰሙትም ሁሉ አስተዋይነቱንና አመላለሱን ያደንቁ ነበር። በአዩትም ጊዜ ደነገጡ፤ እናቱም፥ “ልጄ፥ ለምን እንዲህ አደረግኸን? እነሆ አባትህም፥ እኔም ስንፈልግህ ደከምን” አለችው።
ሉቃስ 2:21-48 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ። በሙሴ ሕግ መሠረት የመንጻታቸው ወቅት በተፈጸመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤ ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር። በዚያ ጊዜ ጻድቅና ትጉህ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረ ሰው ነበር። ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤ እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣ ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ቃል በገባኸው መሠረት፣ አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው፤ ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፣ ማዳንህን አይተዋልና። ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።” አባቱና እናቱም ስለ እርሱ በተነገረው ነገር ተገረሙ። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መውደቅና መነሣት ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኗል፤ የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል።” ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋራ ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤ ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች። በዚያም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች። ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም እያደገ፣ እየጠነከረም ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በርሱ ላይ ነበረ። ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። ዐብሯቸው ያለ መስሏቸው የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያደምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔ እኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።
ሉቃስ 2:21-48 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ፦ የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ፦ ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበረ፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም፦ እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት። ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሁሉንም እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር። የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁ ነበር። ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ። ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው።
ሉቃስ 2:21-48 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከስምንት ቀን በኋላ ሕፃኑ በሚገረዝበት ሥነ ሥርዓት ላይ፥ ስሙ “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ። ይህም ገና ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ያወጣለት ስም ነው። በሕግ መሠረት፥ የመንጻት ሥርዓት የሚፈጸምበት ጊዜ ደረሰ፤ ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን በጌታ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄዱ። ይህንንም ያደረጉት በጌታ ሕግ “ወንድ የሆነ በኲር ልጅ ሁሉ ለጌታ ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል” የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለ ነበር ነው። እንዲሁም በጌታ ሕግ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለመሥዋዕት ማቅረብ ይገባል” የሚል ትእዛዝ ነበረ። በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ጻድቅ ሰው ነበር፤ የእስራኤልን የመዳን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር። እርሱ የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። በዚያን ቀን መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ዮሴፍና ማርያምም በሕጉ መሠረት የተለመደውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ በገቡ ጊዜ ስምዖን ሕፃኑን ተቀብሎ ዐቅፎ፥ እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ የሰጠኸኝ የተስፋ ቃል ተፈጸመ፤ እንግዲህ አሁን እኔን አገልጋይህን በሰላም አሰናብተኝ፤ ማዳንህን በዐይኔ አይቻለሁ፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ እርሱ ለአሕዛብ እውነትን የሚገልጥ ብርሃን ይሆናል፤ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና ማርያም ስለ ሕፃኑ በተባለው ነገር ሁሉ ይደነቁ ነበር። ስምዖን ከባረካቸው በኋላ በተለይ የሕፃኑን እናት ማርያምን እንዲህ አላት፦ “እነሆ! ይህ ሕፃን በእስራኤል ውስጥ ለብዙዎቹ የመጥፋት፥ ለብዙዎቹ ግን የመዳን ምክንያት ይሆናል፤ እርሱም ብዙዎች የማይቀበሉት ምልክት ይሆናል። በዚህም በብዙዎች ልብ ያለው ስውር ሐሳብ ይገለጣል፤ የአንቺንም ልብ የሐዘን ሰይፍ ሰንጥቆት ያልፋል።” እንዲሁም በዚያን ጊዜ ከአሴር ነገድ የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች። በዕድሜዋም በጣም የገፋች ሴት ነበረች፤ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ከተቀመጠች በኋላ ባልዋ ሞተባት፤ ከዚህም በኋላ ዕድሜዋ ሰማኒያ አራት ዓመት እስኪሆን ድረስ ከቤተ መቅደስ ሳትለይ በጾምና በጸሎት ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ታገለግል ነበር። በዚያኑ ጊዜ እርስዋም መጥታ ጌታን ታመሰግን ጀመር፤ ስለ ሕፃኑም የኢየሩሳሌምን መዳን በተስፋ ለሚጠባበቁ ሁሉ ትናገር ነበር። በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሥርዓት ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብም የተሞላ ሆነ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ ከእርሱ ጋር ነበረ። ዮሴፍና ማርያም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። ኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነውም ጊዜ እንደ ተለመደው በዓሉን ለማክበር ሄዱ። በዓሉ ከተፈጸመ በኋላ እነርሱ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ዮሴፍና ማርያም ግን እዚያ መቅረቱን አላወቁም ነበር። ከመንገደኞች ጋር አብሮ የሚሄድ መስሎአቸው የአንድ ቀን መንገድ ሲጓዙ ዋሉ፤ ከዚያም በኋላ ከዘመዶቻቸውና ከሚያውቋቸው ሰዎች ዘንድ ይፈልጉት ጀመር። ነገር ግን ሊያገኙት ስላልቻሉ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በቤተ መቅደስ አገኙት፤ በዚያም በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄም ሲያቀርብላቸው ነበር። የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይገረሙ ነበር። ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደስ ባዩት ጊዜ ተደነቁ፤ በዚያን ጊዜ እናቱ፥ “ልጄ ምነው እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።
ሉቃስ 2:21-48 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስምንት ቀን በሞላውና የመገረዣው ጊዜ ሲደርስ፥ ከመጸነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስሙ ኢየሱስ ተባለ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ እንዲህም የሆነው በጌታ ሕግ፦ “የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ ነው፤ እንዲሁም በጌታ ሕግ እንደተባለው፦ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት የሚጠብቅ፥ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር። በመንፈስም ተነሣስቶ ወደ መቅደስ መጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ሊያደርጉለት ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና፤ እርሱም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን፥ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባሉት ነገሮች ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፦ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት እንዲሆን ተሾሞአል፤ በዚህም የብዙዎችን የልባቸውን አሳብ የሚገለጥ ይሆናል፤ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል።” ከአሴር ወገንም የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ በዕድሜዋም በጣም የገፋች ነበረች፤ እርሷም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርሷም እስከ ሰማኒያ አራት ዓመቷ ድረስ መበለት ነበረች፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሁሉንም ነገር እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ ጠነከረም፤ ጥበብም ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። ወላጆቹም በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ ዮሴፍና እናቱም አላወቁም ነበር። ነገር ግን ከመንገደኞች ጋር የነበረ መስሏቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፤ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም መካከል ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ እየሰማቸውና እየጠየቃቸው በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሶቹ ተገረሙ። ባዩትም ጊዜ እጅግ ተገረሙ፤ እናቱም፦ “ልጄ ሆይ! ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር እኮ፤” አለችው።