ሉቃስ 16:19-26
ሉቃስ 16:19-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ሐምራዊና ቀጭን በፍታ የለበሰ፣ በየቀኑም በተድላ ደስታ የሚኖር አንድ ሀብታም ሰው ነበረ። በአንጻሩም፣ መላ ሰውነቱ በቍስል የተወረረ አንድ አልዓዛር የሚባል ድኻ በዚህ ሀብታም ሰው ደጃፍ ይተኛ ነበር፤ ከሀብታሙ ሰው ማእድ የወደቀውን ፍርፋሪ እንኳ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም ሳይቀሩ መጥተው ቍስሉን ይልሱ ነበር። “ይህም ድኻ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት። ሀብታሙም ሰው ደግሞ ሞቶ ተቀበረ። በሲኦልም እየተሠቃየ ሳለ ቀና ብሎ ከሩቅ አብርሃምን አየ፤ አልዓዛርንም በዕቅፉ ይዞት አየ። እርሱም፣ ‘አብርሃም አባት ሆይ፤ ራራልኝ፤ በዚህ ነበልባል እየተሠቃየሁ ስለሆነ፣ አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ እባክህ ላክልኝ’ እያለ ጮኸ። “አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ በምድራዊ ሕይወትህ ዘመን መልካም ነገሮችን እንደ ተቀበልህ፣ አልዓዛርም ደግሞ ክፉ ነገሮችን እንደ ተቀበለ አስታውስ፤ አሁን ግን እርሱ እዚህ ሲጽናና፣ አንተ በሥቃይ ላይ ትገኛለህ። ከሁሉም በላይ ከዚህ ወደ እናንተ ለማለፍ የሚፈልጉ እንደማይችሉ፣ እዚያ ያሉትም ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ፣ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል ተደርጓል።’
ሉቃስ 16:19-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ፦ አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። አብርሃም ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ።
ሉቃስ 16:19-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ቀይ ከፋይና ቀጭን ልብስ የሚለብስ አንድ ሀብታም ሰው ነበር፤ እርሱም በየቀኑ በቅንጦት ይኖር ነበር። መላ ሰውነቱ በቊስል የተወረሰ አልዓዛር የሚባል አንድ ድኻ ደግሞ በሀብታሙ ቤት ደጃፍ ተኝቶ ነበር፤ ይህም ድኻ፥ ከሀብታሙ ማእድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ለመመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም እየመጡ ቊስሉን ይልሱ ነበር። “ከዚህም በኋላ ድኻው ሰው ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም አጠገብ ወሰዱት፤ እንዲሁም ሀብታሙ ሰው ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም ሲሠቃይ ሳለ፥ ቀና ብሎ አብርሃምንና አጠገቡም የነበረውን አልዓዛርን በሩቅ አያቸው። ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ ‘አባት አብርሃም ሆይ! እባክህ ራራልኝ! በዚህ በእሳት ነበልባል ውስጥ በብርቱ እሠቃያለሁና የጣቱን ጫፍ በውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ አልዓዛርን ላክልኝ!’ “አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ በምድራዊ ሕይወትህ ዘመን ብዙ መልካም ነገር አግኝተህ እንደ ተደሰትህ አስታውስ፤ አልዓዛር ግን በችግር ላይ ነበር፤ ስለዚህ አሁን እርሱ እዚህ ሲደሰት አንተ ትሠቃያለህ። ከዚህም ሁሉ በላይ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል አለ፤ ስለዚህ ከእኛ ወደ እናንተ፥ ከእናንተም ወደ እኛ መሻገር የሚችል ማንም የለም።’
ሉቃስ 16:19-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ፤ ቀይ ሐርና ነጭ ሐር፥ እጅግም ቀጭን ልብስ ይለብስ ነበር፤ ዘወትርም ተድላና ደስታ ያደርግ ነበር። በቍስል ሕመም ተይዞ በባለጸጋው ደጅ የወደቀ አልዓዛር የሚባል አንድ ድሃም ነበረ። ከባለጸጋው ማዕድ የሚወድቀውንም ፍርፋሪ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም እየመጡ ቍስሉን ይልሱት ነበር። ከዚህም በኋላ ድሃው ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም አጠገብ ወሰዱት፤ ባለጸጋውም ደግሞ ሞተ፤ ተቀበረም፤ በሲኦልም በሥቃይ ሳለ ዐይኖቹን አንሥቶ አብርሃምን ከሩቅ አየው፤ አልዓዛርንም በአጠገቡ ተቀምጦ አየው። ‘አባት አብርሃም ሆይ፥ እዘንልኝ፤ በዚች እሳት እጅግ ተሠቃይቻለሁና፥ ጣቱን ከውኃ ነክሮ ምላሴን ያቀዘቅዝልኝ ዘንድ አልዓዛርን ላከው’ ብሎ ተጣራ። አብርሃም ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ተድላና ደስታ እንዳደረግህ፥ አልዓዛርም እንዲሁ ሁልጊዜ በችጋር እንደ ነበረ ዐስብ፤ አሁን ግን እንዲሁ እርሱ በዚህ ፈጽሞ ተድላና ደስታ ያደርጋል፤ አንተ ግን መከራ ትቀበላለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ማለፍ የሚሹ እንዳይችሉ፥ ከእናንተ ወገን የሆኑትም ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል አለ’
ሉቃስ 16:19-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በሐምራዊና በክት ልብስ የሚሽቀረቀር አንድ ሀብታም ሰው ነበረ፤ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በቅንጦት ይኖር ነበር። አልዓዛር የሚባል አንድ ድኻ ሰው ደግሞ በቁስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከሀብታሙም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቁስሎቹን ይልሱ ነበር። ድኻውም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ሀብታሙም ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ፥ አልዓዛርንም በእቅፉ አየ። እርሱም እየጮኸ ‘አብርሃም አባት ሆይ! ማረኝ፤ በዚህ ነበልባል እሠቃያለሁና የጣቱን ጫፍ በውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ላክልኝ፤’ አለ። አብርሃም ግን ‘ልጄ ሆይ! አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም ነገሮችህን እንደተቀበልህ አስብ፤ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል፤ አንተም ትሠቃያለህ። ከዚህም ሁሉ በላይ ከዚህ ወደ እናንተ ማለፍ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል፤’ አለ።