የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 16:1-18

ሉቃስ 16:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ለደቀ መዛ​ሙ​ርቱ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “መጋቢ የነ​በ​ረው አንድ ባለ​ጸጋ ሰው ነበረ፤ ገን​ዘ​ቡን ሁሉ እን​ደ​ሚ​በ​ትን አድ​ር​ገው በእ​ርሱ ዘንድ ከሰ​ሱት። ጌታ​ውም ጠርቶ፦ ‘በአ​ንተ ላይ የም​ሰ​ማው ይህ ነገር ምን​ድን ነው? እን​ግ​ዲህ ወዲህ ለእኔ መጋቢ ልት​ሆን አት​ች​ል​ምና የመ​ጋ​ቢ​ነ​ት​ህን ሂሳብ አስ​ረ​ክ​በኝ’ አለው። ያም መጋቢ ዐስቦ እን​ዲህ አለ፦ ‘ምን ላድ​ርግ? አሁን ጌታዬ ከመ​ጋ​ቢ​ነቴ ይሽ​ረ​ኛል፤ ማረስ አል​ች​ልም፤ ለመ​ለ​መ​ንም አፍ​ራ​ለሁ። እን​ግ​ዲህ ጌታዬ ከም​ግ​ብ​ናዬ የሻ​ረኝ እንደ ሆነ በቤ​ታ​ቸው ይቀ​በ​ሉኝ ዘንድ የማ​ደ​ር​ገ​ውን እኔ ዐው​ቃ​ለሁ።’ ለጌ​ታ​ውም ዕዳ የሚ​ከ​ፍ​ሉ​ትን ጠራ​ቸው፤ የመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ው​ንም፦ ‘ለጌ​ታዬ የም​ት​ከ​ፍ​ለው ዕዳ ምን ያህል ነው?’ አለው፤ እር​ሱም፦ ‘መቶ ማድጋ ዘይት ነው’ አለው። ‘እነሆ፥ ደብ​ዳ​ቤህ፤ ተቀ​ም​ጠህ አምሳ ማድጋ አለ​ብኝ ብለህ ፈጥ​ነህ ጻፍ’ አለው። ሁለ​ተ​ኛ​ው​ንም፦ ‘አን​ተሳ ለጌ​ታዬ የም​ት​ከ​ፍ​ለው ዕዳ ምን ያህል ነው?’ አለው፤ እር​ሱም፦ ‘መቶ ማድጋ ስንዴ ነው’ አለው፤ ‘እነሆ፥ ደብ​ዳ​ቤህ፤ ተቀ​ም​ጠህ ሰማ​ንያ አለ​ብኝ ብለህ ፈጥ​ነህ ጻፍ’ አለው። ጌታ​ውም ዐመ​ፀ​ኛ​ውን መጋቢ እንደ ብልህ ሰው ስለ ሠራ አመ​ሰ​ገ​ነው፤ ከብ​ር​ሃን ልጆች ይልቅ የዚህ ዓለም ልጆች በዓ​ለ​ማ​ቸው ይራ​ቀ​ቃ​ሉና። እኔም እላ​ች​ኋ​ለሁ፦ ባለ​ቀ​ባ​ችሁ ጊዜ እነ​ርሱ በዘ​ለ​ዓ​ለም ቤታ​ቸው ይቀ​በ​ሉ​አ​ችሁ ዘንድ በዐ​መፃ ገን​ዘብ ለእ​ና​ንተ ወዳ​ጆች አድ​ር​ጉ​በት። “በጥ​ቂት የሚ​ታ​መን በብዙ ይታ​መ​ናል፤ በጥ​ቂት የሚ​ያ​ም​ፅም በብ​ዙም ቢሆን ያም​ፃል። በዐ​መፃ ገን​ዘብ ካል​ታ​መ​ና​ችሁ በእ​ው​ነ​ተ​ኛው ገን​ዘብ ማን ያም​ና​ች​ኋል? በሌ​ላ​ውስ ገን​ዘብ ካል​ታ​መ​ና​ችሁ የራ​ሱን ማን ይሰ​ጣ​ች​ኋል? ለሁ​ለት ጌቶች መገ​ዛት የሚ​ችል አገ​ል​ጋይ የለም፤ ካል​ሆ​ነም አን​ዱን ይወ​ድ​ዳል፤ ሁለ​ተ​ኛ​ው​ንም ይጠ​ላል፤ ወይም ለአ​ንዱ ይታ​ዘ​ዛል፤ ለሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም እንቢ ይላል፤ እን​ዲ​ሁም እና​ንተ ገን​ዘብ እየ​ወ​ደ​ዳ​ችሁ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መገ​ዛት አት​ች​ሉም።” ገን​ዘ​ብን የሚ​ወዱ ፈሪ​ሳ​ው​ያ​ንም ይህን ሁሉ ነገር ሰም​ተው ተጠ​ቃ​ቀ​ሱ​በት። እር​ሱም፥ “እና​ን​ተስ ለሰው ይም​ሰል ትመ​ጻ​ደ​ቃ​ላ​ችሁ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ልቡ​ና​ች​ሁን ያው​ቃል፤ በሰው ዘንድ የከ​በረ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የተ​ናቀ ይሆ​ና​ልና። “ኦሪ​ትም ነቢ​ያ​ትም ከጥ​ንት ጀምሮ እስከ ዮሐ​ንስ ድረስ ነበሩ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት ይሰ​በ​ካል፤ ሁሉም ወደ እር​ስዋ ይጋ​ፋል። ነገር ግን ከኦ​ሪት አን​ዲት ቃል ከም​ት​ወ​ድቅ ሰማ​ይና ምድር ቢያ​ልፍ ይቀ​ላል። “ሚስ​ቱን ፈትቶ ሌላ​ዪ​ቱን የሚ​ያ​ገባ ሁሉ ያመ​ነ​ዝ​ራል፤ ባልዋ የፈ​ታ​ት​ንም የሚ​ያ​ገባ ያመ​ነ​ዝ​ራል።

ሉቃስ 16:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ መጋቢ ነበረው፤ ይኸው መጋቢ የሀብታሙን ሰው ንብረት እንደሚያባክን ለዚሁ ሰው ወሬ ደረሰው። ስለዚህ አስጠራውና፣ ‘ይህ የምሰማብህ ምንድን ነው? ከእንግዲህ አንተ መጋቢ ልትሆነኝ ስለማትችል፣ የምታስተዳድረውን ንብረት መቈጣጠሪያ ሒሳብ አስረክበኝ’ አለው። “መጋቢውም በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ከመጋቢነት ሊሽረኝ ነው፤ ለማረስ ጕልበት የለኝም፤ መለመን ደግሞ ዐፍራለሁ፤ ስለዚህ ምን ላድርግ? ከመጋቢነት የተሻርሁ እንደ ሆነ፣ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን ዐውቃለሁ።’ “ስለዚህ የጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ጠራ፤ የመጀመሪያውንም ሰው ‘የጌታዬ ዕዳ ምን ያህል አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘አንድ መቶ ማድጋ ዘይት አለብኝ’ አለ። “መጋቢውም፣ ‘የውል ወረቀትህን ዕንካ፤ ቶሎ ተቀምጠህ “አምሳ ማድጋ” ብለህ ጻፍ’ አለው። “ከዚያም ሌላውን፣ ‘አንተስ ስንት አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘አምሳ ዳውላ ስንዴ’ አለው። “መጋቢውም፣ ‘የብድር ደብዳቤህን ዕንካ፤ “አርባ ዳውላ” ብለህ ጻፍ’ አለው። “ጌታውም አጭበርባሪውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ከመሰሎቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የዚህ ዓለም ገንዘብ ባለቀ ጊዜ በዘላለም ቤት ተቀባይነት እንዲኖራችሁ፣ በዚሁ ገንዘብ ወዳጆችን ለራሳችሁ አፍሩበት። “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም። እንግዲህ፣ በዚህ ዓለም ሀብት ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውንማ ሀብት ማን ዐደራ ብሎ ይሰጣችኋል? በሌላው ሰው ሀብት ካልታመናችሁ፣ የራሳችሁ የሆነውን ሀብት ማን ይሰጣችኋል? “በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም ባሪያ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን ይጠጋል፤ ሌላውን ይንቃል። የእግዚአብሔርም የገንዘብም ባሪያ መሆን አትችሉም።” ገንዘብ የሚወድዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው በኢየሱስ ላይ አፌዙበት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በሰዎች ፊት ራሳችሁን የምታጸድቁ ናችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል፤ በሰዎች ዘንድ የከበረ፣ በእግዚአብሔር ፊት የረከሰ ነውና። “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ኖረዋል፤ ከዚያ በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ተሰብኳል፤ ሰውም ሁሉ ወደዚያ ለመግባት ይሻማል። ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀልላል። “ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ከባሏ የተፋታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”

ሉቃስ 16:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ በእርሱ ዘንድ፦ ይህ ሰው ያለህን ይበትናል ብለው ከሰሱት። ጠርቶም፦ ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ አለው። መጋቢውም በልቡ፦ ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፥ መለመንም አፍራለሁ። ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ አለ። የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የፊተኛውን፦ ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ? አለው። እርሱም፦ መቶ ማድጋ ዘይት አለ። ደብዳቤህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ አምሳ ብለህ ጻፍ አለው። በኋላም ሌላውን፦ አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ? አለው። እርሱም፦ መቶ ጫን ስንዴ አለ። ደብዳቤህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ አለው። ጌታውም ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና። እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። እንዲህም አላቸው፦ ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና። ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ በኃይል ይገቡባታል። ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል። ሚስቱንም የሚፈታ ሁሉ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፥ ከባልዋም የተፈታችውን የሚያገባ ያመነዝራል።

ሉቃስ 16:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደግሞም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው ቤቱን የሚያስተዳድርለት መጋቢ ነበረው፤ ሰዎች ‘ይህ መጋቢ ንብረትህን ያባክናል’ ብለው ለሀብታሙ ሰው ከሰሱት። ሀብታሙም ሰው መጋቢውን አስጠርቶ ‘ይህ የምሰማብህ ነገር ምንድን ነው? ከእንግዲህ ወዲህ መጋቢዬ ልትሆን አትችልምና በመጋቢነትህ የሠራህበትን የንብረቴን ሒሳብ አቅርብልኝ’ አለው። መጋቢውም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘አሁን እንግዲህ ጌታዬ ከመጋቢነት ሥራዬ ሊያሰናብተኝ ነው፤ ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል? ለመቈፈር ዐቅም የለኝም፤ አልችልም፤ መለመን ደግሞ ያሳፍረኛል፤ ቈይ! የማደርገውን ዐውቃለሁ፤ ከመጋቢነት ሥራዬ ስሰናበት፥ በቤታቸው የሚቀበሉኝ ወዳጆች እንዲኖሩኝ አደርጋለሁ።’ “ስለዚህ የጌታውን ባለዕዳዎች ሁሉ አንድ በአንድ ጠርቶ፥ የመጀመሪያውን ‘ለጌታዬ የምትከፍለው ምን ያኽል ዕዳ አለብህ?’ ሲል ጠየቀው፤ እርሱም ‘መቶ ማድጋ ዘይት ዕዳ አለብኝ’ አለ፤ መጋቢው ‘የፈረምከው ውል ይኸውልህ ቶሎ ተቀመጥና ኀምሳ ማድጋ ብለህ ጻፍ’ አለው። ሁለተኛውንም ጠርቶ፥ ‘የአንተስ ዕዳ ምን ያኽል ነው?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ዳውላ ስንዴ ዕዳ አለብኝ’ ሲል መለሰ። መጋቢውም ‘ይኸው የፈረምከው ውል! ሰማኒያ ዳውላ ብለህ ጻፍ’ አለው። ጌታውም እምነት ያጐደለውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ሰዎች ይልቅ የዓለም ሰዎች በዓለማዊ ኑሮአቸው ብልኆች መሆናቸውን ያሳያል። “ስለዚህ በዐመፅ ገንዘብ ወዳጆች አብጁ እላችኋለሁ፤ ይህን ብታደርጉ ገንዘባችሁ አልቆባችሁ ባዶ እጃችሁን ስትቀሩ ወዳጆቻችሁ ለዘለዓለም በሚኖሩበት ቤት ይቀበሉአችኋል። በትንሽ ነገር የታመነ ሰው በትልቅ ነገርም የታመነ ይሆናል፤ በትንሽ ነገር የማይታመን ሰው ግን በትልቅ ነገርም አይታመንም። ታዲያ የዚህን ዓለም ሀብት በማስተዳደር የማትታመኑ ከሆናችሁ እውነተኛውን ሀብትማ ማን አምኖ ይሰጣችኋል? ደግሞም በሌላው ሰው ሀብት የማትታመኑ ከሆነ ለእናንተ የሚሆነውንስ ሀብት ማን ይሰጣችኋል? “አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌታ ማገልገል አይችልም፤ ይህ ከሆነ፥ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ አንዱን አክብሮ፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ ልትገዙ አትችሉም።” ፈሪሳውያን ገንዘብ ወዳዶች ስለ ነበሩ፥ ኢየሱስ የተናገረውን ሁሉ ሰምተው አፌዙበት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ራሳችሁን በሰው ፊት ጻድቅ ታስመስላላችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ፊት ክብር ያለው መስሎ የሚታይ፥ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።” ኢየሱስ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “የሕግና የነቢያት መጻሕፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ቈይተው ነበር፤ ከዚያም ወዲህ የሚነገረው የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ቃል ነው፤ እያንዳንዱም ሰው ወደዚያች መንግሥት ለመግባት ብርቱ ጥረት ያደርጋል። ይሁን እንጂ፥ ከሕግ አንዲቱ ነጥብ እንኳ ከምትጠፋ ሰማይና ምድር ቢያልፉ ይቀላል። “ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ እንዲሁም ከባልዋ የተፋታችውን ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”

ሉቃስ 16:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “መጋቢ የሚያገለግለው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፤ ‘ይህ ሰው ያለህን ይበትናል፤’ የሚል ክስ በእርሱ ዘንድ አቀረቡ። ጠርቶም ‘ይህ የምሰማብህ ነገር ምንድነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ፤’ አለው። መጋቢውም በልቡ ‘ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፤ መለመንም አፍራለሁ። ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ፤’ አለ። የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የመጀመሪያውን ‘ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ማድጋ ዘይት’ አለ። ‘የጽሑፍ ማስረጃህን እንካ፥ ፈጥነህም ተቀምጠና ኀምሳ ብለህ ጻፍ፤’ አለው። በኋላም ሌላውን ‘አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ዳውላ ስንዴ’ አለ። ‘የጽሑፍ ማስረጃህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ፤’ አለው። ጌታውም ዐመፀኛውን መጋቢ ስለ ብልኃቱ አመሰገነው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና። እኔም እላችኋለሁ፤ የዐመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘለዓለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ አማካኝነት ወዳጆችን ለራሳችሁ አብጁ። “በትንሹ የታመነ በብዙም እንዲሁ የታመነ ነው፤ በትንሹ የሚያታልል በብዙም እንዲሁ ያታልላል። እንግዲያስ በዐመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አንድም አገልጋይ የለም፤ ወይ አንዱን ሲጠላ ሌላውን ይወዳል፤ ወይ አንዱን ሲጠጋ ሌላውን ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። እንዲህም አላቸው “ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሰት ነውና። “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርሷ ለመግባት ይታገላል። ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል። “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ባልዋም የፈታትን የሚያገባ ያመነዝራል።