ደግሞም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው ቤቱን የሚያስተዳድርለት መጋቢ ነበረው፤ ሰዎች ‘ይህ መጋቢ ንብረትህን ያባክናል’ ብለው ለሀብታሙ ሰው ከሰሱት። ሀብታሙም ሰው መጋቢውን አስጠርቶ ‘ይህ የምሰማብህ ነገር ምንድን ነው? ከእንግዲህ ወዲህ መጋቢዬ ልትሆን አትችልምና በመጋቢነትህ የሠራህበትን የንብረቴን ሒሳብ አቅርብልኝ’ አለው። መጋቢውም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘አሁን እንግዲህ ጌታዬ ከመጋቢነት ሥራዬ ሊያሰናብተኝ ነው፤ ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል? ለመቈፈር ዐቅም የለኝም፤ አልችልም፤ መለመን ደግሞ ያሳፍረኛል፤ ቈይ! የማደርገውን ዐውቃለሁ፤ ከመጋቢነት ሥራዬ ስሰናበት፥ በቤታቸው የሚቀበሉኝ ወዳጆች እንዲኖሩኝ አደርጋለሁ።’ “ስለዚህ የጌታውን ባለዕዳዎች ሁሉ አንድ በአንድ ጠርቶ፥ የመጀመሪያውን ‘ለጌታዬ የምትከፍለው ምን ያኽል ዕዳ አለብህ?’ ሲል ጠየቀው፤ እርሱም ‘መቶ ማድጋ ዘይት ዕዳ አለብኝ’ አለ፤ መጋቢው ‘የፈረምከው ውል ይኸውልህ ቶሎ ተቀመጥና ኀምሳ ማድጋ ብለህ ጻፍ’ አለው። ሁለተኛውንም ጠርቶ፥ ‘የአንተስ ዕዳ ምን ያኽል ነው?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ዳውላ ስንዴ ዕዳ አለብኝ’ ሲል መለሰ። መጋቢውም ‘ይኸው የፈረምከው ውል! ሰማኒያ ዳውላ ብለህ ጻፍ’ አለው። ጌታውም እምነት ያጐደለውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ሰዎች ይልቅ የዓለም ሰዎች በዓለማዊ ኑሮአቸው ብልኆች መሆናቸውን ያሳያል። “ስለዚህ በዐመፅ ገንዘብ ወዳጆች አብጁ እላችኋለሁ፤ ይህን ብታደርጉ ገንዘባችሁ አልቆባችሁ ባዶ እጃችሁን ስትቀሩ ወዳጆቻችሁ ለዘለዓለም በሚኖሩበት ቤት ይቀበሉአችኋል። በትንሽ ነገር የታመነ ሰው በትልቅ ነገርም የታመነ ይሆናል፤ በትንሽ ነገር የማይታመን ሰው ግን በትልቅ ነገርም አይታመንም። ታዲያ የዚህን ዓለም ሀብት በማስተዳደር የማትታመኑ ከሆናችሁ እውነተኛውን ሀብትማ ማን አምኖ ይሰጣችኋል? ደግሞም በሌላው ሰው ሀብት የማትታመኑ ከሆነ ለእናንተ የሚሆነውንስ ሀብት ማን ይሰጣችኋል? “አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌታ ማገልገል አይችልም፤ ይህ ከሆነ፥ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ አንዱን አክብሮ፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ ልትገዙ አትችሉም።” ፈሪሳውያን ገንዘብ ወዳዶች ስለ ነበሩ፥ ኢየሱስ የተናገረውን ሁሉ ሰምተው አፌዙበት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ራሳችሁን በሰው ፊት ጻድቅ ታስመስላላችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ፊት ክብር ያለው መስሎ የሚታይ፥ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።” ኢየሱስ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “የሕግና የነቢያት መጻሕፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ቈይተው ነበር፤ ከዚያም ወዲህ የሚነገረው የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ቃል ነው፤ እያንዳንዱም ሰው ወደዚያች መንግሥት ለመግባት ብርቱ ጥረት ያደርጋል። ይሁን እንጂ፥ ከሕግ አንዲቱ ነጥብ እንኳ ከምትጠፋ ሰማይና ምድር ቢያልፉ ይቀላል። “ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ እንዲሁም ከባልዋ የተፋታችውን ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”
የሉቃስ ወንጌል 16 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 16:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos