ሉቃስ 12:54-59
ሉቃስ 12:54-59 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፥ “ደመና በምዕራብ በኩል ደምኖ ባያችሁ ጊዜ ‘ዝናም ይመጣል’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል። የአዜብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜም ‘ድርቅ ይሆናል፤’ ትላላችሁ እንዲሁም ይሆናል። እናንት ግብዞች! የሰማዩንና የምድሩን ፊት መመርመር ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እነዚህን ዘመናት መመርመርን እንዴት አታውቁም? እናንተ ራሳችሁ እውነቱን ለምን አትፈርዱም? ከባለጋራህ ጋር ወደ ሹም በምትሄድበት ጊዜ ወደ ዳኛ እንዳይወስድህ በመንገድ ሳለህ ታረቅ፤ ዕዳህንም ክፈል፤ ዳኛው ለሎሌው አሳልፎ ይሰጥሃልና። ሎሌውም በወኅኒ ቤት ያስርሃል። ያለብህን የመጨረሻዋን ግማሽ ሣንቲም ቢሆን እስክትጨርስ ድረስ አትወጣም እልሃለሁ።”
ሉቃስ 12:54-59 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ደግሞም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ደመና በምዕራብ በኩል ሲወጣ ስታዩ ወዲያው፣ ዝናብ ሊመጣ ነው ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል፤ የደቡብ ነፋስም ከደቡብ በኩል ሲነፍስ፣ ቀኑ ሞቃት ይሆናል ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል። እናንት ግብዞች፤ የምድሩንና የሰማዩን መልክ መመርመር ታውቁበታላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መመርመር እንዴት ተሳናችሁ? “ታዲያ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? ከባላጋራህ ጋር ወደ ዳኛ ፊት ለመቅረብ ስትሄድ፣ ገና በመንገድ ላይ ሳለህ ለመታረቅ ጥረት አድርግ፤ አለዚያ ጐትቶ ወደ ዳኛው ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለመኰንኑ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኰንኑም ወደ ወህኒ ይጥልሃል። እልሃለሁ፤ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።”
ሉቃስ 12:54-59 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው፦ ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፥ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ፦ ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፥ ይሆንማል። እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? ራሳችሁ ደግሞ ጽድቅን የማትፈርዱ ስለ ምን ነው? ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ። እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።
ሉቃስ 12:54-59 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ደግሞም ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ደመና በስተ ምዕራብ በኩል ስታዩ ወዲያውኑ፦ ‘እነሆ! ዛሬ ሊዘንብ ነው!’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይዘንባል። እንዲሁም ነፋስ በስተ ደቡብ በኩል በሚነፍስበት ጊዜ፥ ‘ዛሬ ሙቀት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይሆናል። እናንተ ግብዞች የምድሩንና የሰማዩን መልክ በመመልከት የሚሆነውን ታውቃላችሁ፤ ታዲያ በዚህ በአሁኑ ዘመን የሚሆነውን ለምን አታውቁም?” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ስለምን እናንተ ራሳችሁ ትክክለኛውን ነገር ዐውቃችሁ አትፈርዱም? ባላጋራህ ከሶህ ወደ ፍርድ ቤት በሚወስድህ ጊዜ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ለመስማማት ተጣጣር፤ አለበለዚያ እርሱ ወደ ዳኛ ጐትቶ ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለአሳሪው አሳልፎ ይሰጥሃል፤ አሳሪውም ወደ እስር ቤት ያገባሃል። መቀጮህን ሁሉ ጨርሰህ ሳትከፍል ከእስር ቤት መውጣት እንደማትችልም እነግርሃለሁ።”
ሉቃስ 12:54-59 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ “ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው ‘ዝናብ ይመጣል፤’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ ‘ትኩሳት ይሆናል፥’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል። እናንት ግብዞች! የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? “እናንተ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ለመታረቅ ትጋ። የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።”