የሉቃስ ወንጌል 12
12
ከፈሪሳውያን እርሾ ስለ መጠበቅ
(ማቴ. 10፥26-27)
1 #
ማቴ. 16፥6፤ ማር. 8፥15። በዚያን ጊዜ፥ በሺዎች የሚቈጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ከብዛታቸው የተነሣ እየተረጋገጡ ሳለ፥ በቅድሚያ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፦ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ፤ እርሱም ግብዝነት ነው። 2#ማር. 4፥22፤ ሉቃ. 8፥17።የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። 3ስለዚህ በጨለማ የተናገራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይታወጃል።
ማንን መፍራት እንደሚገባ
(ማቴ. 10፥28-31)
4ለእናንተም ለወዳጆቼ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ሥጋን የሚገድሉትን፥ ከዚያ አልፈው ግን ፈጽሞ ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ። 5ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ እርሱን ፍሩ። 6አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱ አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። 7ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቆጠረ ነው፤ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።
ስለ ክርስቶስ መመስከር
(ማቴ. 10፥19-20፤32-33፤ 12፥32)
8“እላችኋለሁ፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤ 9በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። 10#ማቴ. 12፥32፤ ማር. 3፥29።በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም። 11#ማቴ. 10፥19፤20፤ ማር. 13፥11፤ ሉቃ. 21፥14፤15።ወደ ምኵራቦች፥ ወደ ገዢዎችና ወደ ባለ ሥልጣኖች ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንደምትመልሱ ወይም እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ 12መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።”
የሞኙ ባለጸጋ ምሳሌ
13ከሕዝቡም አንድ ሰው “መምህር ሆይ! ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው፤” አለው። 14እርሱም “አንተ ሰው! ለዳኝነትና ለማከፋፈል ማን ነው በላያችሁ የሾመኝ?” አለው። 15“የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፤ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ፤” አላቸው። 16ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል “አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያማ ሆነችለት። 17እርሱም ‘ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ?’ ብሎ በልቡ አሰበ። 18‘እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጎተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፤ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19#ሲራ. 11፥19።ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ! ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስ ይበልሽ እላታለሁ፤’ አለ። 20እግዚአብሔር ግን ‘አንተ ሰነፍ! በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል?’ አለው። 21ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።”
ለምግብና ለልብስ መጨነቅ እንደማይገባ
(ማቴ. 6፥25-34)
22ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። 23ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፤ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? 25ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? 26እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? 27#1ነገ. 10፥4-7፤ 2ዜ.መ. 9፥3-6።አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። 28እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? 29እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፤ 30ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። 31ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
በምድር ላይ ሀብት ማከማቸት እንደማይገባ
(ማቴ. 6፥19-21)
32“አንተ ታናሽ መንጋ! መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። 33ያላችሁን ሽጡ፤ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ 34መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
ትጉህ አገልጋዮች
35 #
ማቴ. 25፥1-13። “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ 36#ማር. 13፥34-36።እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ፤ 37ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። 38ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው። 39#ማቴ. 24፥43፤44።ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። 40እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።”
41ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን?” አለው። 42ጌታም አለ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? 43ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ ብፁዕ ነው። 44እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 45ያ ባርያ ግን ‘ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል’ ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ 46የዚያ ባርያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፤ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። 47የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደሱም ፈቃድ ያላደረገ ያ ባርያ እጅግ ይገረፋል 48ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።
ሁሉን ነገር ትቶ ኢየሱስን መከተል
(ማቴ. 10፥34-36)
49“በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ፤ አሁን ቢቀጣጠል ምንኛ በወደድሁ? 50#ማር. 10፥38።ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፤ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ? 51በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፤ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ። 52ከአሁን ጀምሮ በአንዲት ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉና፤ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። 53#ሚክ. 7፥6።አባት በልጁ ላይ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በልጇ ላይ ልጇም በእናትዋ ላይ፥ አማት በምራትዋ ላይ ምራትም በአማትዋ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።”
54ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ “ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው ‘ዝናብ ይመጣል፤’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል፤ 55በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ ‘ትኩሳት ይሆናል፥’ ትላላችሁ፤ እንዲሁም ይሆናል። 56እናንት ግብዞች! የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው?
57“እናንተ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? 58ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ለመታረቅ ትጋ። 59የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።”
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 12: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ