ሉቃስ 12:24-34

ሉቃስ 12:24-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የማ​ይ​ዘ​ሩ​ት​ንና የማ​ያ​ጭ​ዱ​ትን፥ ጎተ​ራና ጕድ​ጓድ የሌ​ላ​ቸ​ውን የቍ​ራ​ዎ​ችን ጫጭ​ቶች ተመ​ል​ከቱ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን ይመ​ግ​ባ​ቸ​ዋል፤ እን​ግ​ዲህ እና​ንተ ከወ​ፎች እን​ዴት እጅግ አት​በ​ል​ጡም? ከእ​ና​ን​ተስ ዐስቦ በቁ​መቱ ላይ አንድ ክንድ መጨ​መር የሚ​ቻ​ለው ማነው? ይህን ቀላ​ሉን የማ​ት​ችሉ ከሆነ በሌ​ላው ለምን ትጨ​ነ​ቃ​ላ​ችሁ? እነሆ፥ አበ​ባ​ዎ​ችን እን​ደ​ሚ​ያ​ድጉ ተመ​ል​ከቱ፤ አይ​ፈ​ት​ሉም፤ አይ​ደ​ክ​ሙም፤ ነገር ግን እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ሰሎ​ሞን እንኳ በክ​ብሩ ዘመን ሁሉ ከእ​ነ​ርሱ እንደ አንዱ አል​ለ​በ​ሰም። እነሆ፥ ዛሬ ያለ​ውን፥ ነገም ወደ እሳት የሚ​ጣ​ለ​ውን የአ​በባ አገዳ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ የሚ​ያ​ደ​ር​ገው ከሆነ፥ እና​ንተ እም​ነት የጐ​ደ​ላ​ችሁ፥ ለእ​ና​ን​ተማ እን​ዴት አብ​ልጦ አያ​ደ​ር​ግ​ላ​ችሁ? እና​ን​ተም የም​ት​በ​ሉ​ት​ንና የም​ት​ጠ​ጡ​ትን አት​ፈ​ልጉ፤ ወዲ​ያና ወዲ​ህም አት​በሉ፤ አት​ጨ​ነ​ቁ​ለ​ትም። ይህን ሁሉ በውጭ ያሉ የዓ​ለም አሕ​ዛብ ይሹ​ታ​ልና፤ ለእ​ና​ን​ተስ አባ​ታ​ችሁ ይህን ሁሉ እን​ደ​ም​ት​ሹት ያው​ቃል። ነገር ግን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ግ​ሥ​ትና ጽድቅ ሹ፤ ይህም ሁሉ ይጨ​መ​ር​ላ​ች​ኋል። “አንተ ታናሽ መንጋ፥ አት​ፍራ፤ አባ​ታ​ችሁ መን​ግ​ሥ​ቱን ሊሰ​ጣ​ችሁ ወዶ​አ​ልና። ሀብ​ታ​ች​ሁን ሸጣ​ችሁ ምጽ​ዋት ስጡ፤ ሌባ በማ​ያ​ገ​ኝ​በት ነቀ​ዝም በማ​ያ​በ​ላ​ሽ​በት፥ የማ​ያ​ረጅ ከረ​ጢት፥ የማ​ያ​ል​ቅም መዝ​ገብ በሰ​ማ​ያት ለእ​ና​ንተ አድ​ርጉ። መዝ​ገ​ባ​ችሁ ካለ​በት ልባ​ችሁ በዚያ ይኖ​ራ​ልና።

ሉቃስ 12:24-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ? “እስኪ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ አትሹ፤ አትጨነቁም፤ ይህንማ በዓለም ያሉ ሰዎች ሁሉ አጥብቀው ይሻሉ፤ አባታችሁም እነዚህ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ይጨመሩላችኋል። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤ ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ሀብት በሰማይ አከማቹ፤ ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይሆናልና።

ሉቃስ 12:24-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።

ሉቃስ 12:24-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እስቲ ቊራዎችን ተመልከቱ! እነርሱ አይዘሩም ወይም አያጭዱም፤ የእህል ማከማቻ ቦታ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች የቱን ያኽል ትበልጣላችሁ! ለመሆኑ ከእናንተ መካከል በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ይህን ትንሹን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላው ነገር ትጨነቃላችሁ? የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ ይሁን እንጂ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ ያጌጠ ልብስ አለበሰም። ታዲያ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ አስጊጦ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም! “ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። ይህን ለማግኘትማ የዚህ ዓለም ሰዎችም ይጨነቁበታል፤ እናንተ ግን ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። ይልቅስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይጨመሩላችኋል። “እናንተ እንደ ታናናሽ መንጋ የሆናችሁ ወገኖቼ አትፍሩ፤ የሰማይ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ፈቅዶአል። ያላችሁን ሁሉ ሸጣችሁ ገንዘቡን ለድኾች ስጡ፤ የማያረጅ የገንዘብ ቦርሳም አዘጋጅታችሁ ገንዘባችሁን ሌባ በማይደርስበት፥ ብል በማይበላበትና ከቶም በማያልቅበት ቦታ በመንግሥተ ሰማያት አስቀምጡ። ገንዘባችሁ ባለበት ቦታ ልባችሁም በዚያው ይሆናል።”

ሉቃስ 12:24-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፤ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። “አንተ ታናሽ መንጋ! መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ፤ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።