ሉቃስ 12:22-31
ሉቃስ 12:22-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፥ “ስለዚህ እላችህዋለሁ፤ ለነፍሳችሁ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት፥ ለሰውነታችሁም ስለምትለብሱት አትጨነቁ። ነፍስ ከምግብ ትበልጣለችና፤ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። የማይዘሩትንና የማያጭዱትን፥ ጎተራና ጕድጓድ የሌላቸውን የቍራዎችን ጫጭቶች ተመልከቱ፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል፤ እንግዲህ እናንተ ከወፎች እንዴት እጅግ አትበልጡም? ከእናንተስ ዐስቦ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚቻለው ማነው? ይህን ቀላሉን የማትችሉ ከሆነ በሌላው ለምን ትጨነቃላችሁ? እነሆ፥ አበባዎችን እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይፈትሉም፤ አይደክሙም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ዘመን ሁሉ ከእነርሱ እንደ አንዱ አልለበሰም። እነሆ፥ ዛሬ ያለውን፥ ነገም ወደ እሳት የሚጣለውን የአበባ አገዳ እግዚአብሔር እንዲህ የሚያደርገው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ ለእናንተማ እንዴት አብልጦ አያደርግላችሁ? እናንተም የምትበሉትንና የምትጠጡትን አትፈልጉ፤ ወዲያና ወዲህም አትበሉ፤ አትጨነቁለትም። ይህን ሁሉ በውጭ ያሉ የዓለም አሕዛብ ይሹታልና፤ ለእናንተስ አባታችሁ ይህን ሁሉ እንደምትሹት ያውቃል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ ሹ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
ሉቃስ 12:22-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማነው? እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ? “እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ በመሻት ልባችሁ አይጨነቅ፤ ይህንማ በዓለም ያለ ሕዝብ ሁሉ ይፈልጋል፤ አባታችሁ እኮ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል። ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ በተጨማሪ ይሰጣችኋል።
ሉቃስ 12:22-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
ሉቃስ 12:22-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ ለሕወታችሁ ‘ምን እንበላለን? ለሰውነታችሁም ምን እንለብሳለን?’ በማለት ስለ ኑሮአችሁ አትጨነቁ እላችኋለሁ። ከምግብ ሕይወት፥ ከልብስም ሰውነት ይበልጣል። እስቲ ቊራዎችን ተመልከቱ! እነርሱ አይዘሩም ወይም አያጭዱም፤ የእህል ማከማቻ ቦታ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች የቱን ያኽል ትበልጣላችሁ! ለመሆኑ ከእናንተ መካከል በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ይህን ትንሹን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላው ነገር ትጨነቃላችሁ? የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ ይሁን እንጂ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ ያጌጠ ልብስ አለበሰም። ታዲያ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ አስጊጦ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም! “ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። ይህን ለማግኘትማ የዚህ ዓለም ሰዎችም ይጨነቁበታል፤ እናንተ ግን ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። ይልቅስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይጨመሩላችኋል።
ሉቃስ 12:22-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፤ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።