ሉቃስ 1:8-30

ሉቃስ 1:8-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እር​ሱም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በተ​ራው የክ​ህ​ነ​ትን ሥራ በሚ​ሠ​ራ​በት ጊዜ፥ ካህ​ናት እን​ደ​ሚ​ያ​ደ​ር​ጉት የሚ​ያ​ጥ​ን​በት ጊዜ ደረሰ፤ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤተ መቅ​ደ​ስም ገባ። ዕጣን በሚ​ያ​ጥ​ን​በት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸ​ልዩ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አ​ክም በዕ​ጣን መሠ​ው​ያው በስ​ተ​ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካ​ር​ያ​ስም ባየው ጊዜ ደነ​ገጠ፤ ፍር​ሀ​ትም ረዓ​ድም ወረ​ደ​በት። መል​አ​ኩም እን​ዲህ አለው፥ “ዘካ​ር​ያስ ሆይ፥ አት​ፍራ፤ ጸሎ​ትህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ተሰ​ም​ቶ​አ​ልና፤ ሚስ​ትህ ኤል​ሣ​ቤ​ጥም ትፀ​ን​ሳ​ለች፤ ወንድ ልጅ​ንም ትወ​ል​ድ​ል​ሃ​ለች፤ ስሙ​ንም ዮሐ​ንስ ትለ​ዋ​ለህ። ደስ​ታና ሐሤ​ትም ይሆ​ን​ል​ሃል፤ በመ​ወ​ለ​ዱም ብዙ​ዎች ደስ ይላ​ቸ​ዋል። እርሱ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ታላቅ ይሆ​ና​ልና የወ​ይን ጠጅና የሚ​ያ​ሰ​ክ​ርም መጠጥ ሁሉ አይ​ጠ​ጣም፤ ከእ​ናቱ ማሕ​ፀን ጀም​ሮም መን​ፈስ ቅዱስ ይመ​ላ​በ​ታል። ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ብዙ​ዎ​ችን ወደ አም​ላ​ካ​ቸው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ል​ሳ​ቸ​ዋል። እር​ሱም የአ​ባ​ቶ​ችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከ​ሓ​ድ​ያ​ን​ንም ዐሳብ ወደ ጻድ​ቃን ዕው​ቀት ይመ​ልስ ዘንድ፥ ሕዝ​ብ​ንም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ዘ​ጋጀ ያደ​ርግ ዘንድ በኤ​ል​ያስ መን​ፈ​ስና ኀይል በፊቱ ይሄ​ዳል።” ዘካ​ር​ያ​ስም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ እን​ዲህ አለው፥ “ይህ እን​ደ​ሚ​ሆን በምን አው​ቃ​ለሁ? እነሆ፥ እኔ አር​ጅ​ች​አ​ለሁ፤ የሚ​ስ​ቴም ዘመ​ንዋ አል​ፏል።” መል​አ​ኩም መልሶ እን​ዲህ አለው፥ “እኔ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት የም​ቆ​መው ገብ​ር​ኤል ነኝ፤ ይህ​ንም እነ​ግ​ር​ህና አበ​ሥ​ርህ ዘንድ ወደ አንተ ተል​ኬ​አ​ለሁ። አሁ​ንም በጊ​ዜው የሚ​ሆ​ነ​ው​ንና የሚ​ፈ​ጸ​መ​ውን ነገ​ሬን አላ​መ​ን​ኽ​ኝ​ምና ይህ እስ​ኪ​ሆን ድረስ ዲዳ ትሆ​ና​ለህ፤ መና​ገ​ርም ይሳ​ን​ሃል።” ሕዝቡ ግን ዘካ​ር​ያ​ስን ይጠ​ብ​ቁት ነበር፤ በቤተ መቅ​ደስ ውስጥ ዘግ​ይቶ ነበ​ርና እጅግ ተደ​ነቁ። ወደ እነ​ርሱ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜም እነ​ር​ሱን ማነ​ጋ​ገር ተሳ​ነው፤ በቤተ መቅ​ደ​ስም የተ​ገ​ለ​ጠ​ለት እን​ዳለ ዐወቁ፤ እን​ዲ​ሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያ​መ​ለ​ከ​ታ​ቸው ኖረ። ከዚ​ህም በኋላ የማ​ገ​ል​ገሉ ወራት በተ​ፈ​ጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ። ከእ​ነ​ዚ​ያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤል​ሳ​ቤጥ ፀነ​ሰች፤ ፅን​ስ​ዋ​ንም ለአ​ም​ስት ወር ሸሸ​ገች፤ እን​ዲህ ስትል፦ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድ​ቤን ያርቅ ዘንድ በጐ​በ​ኘኝ ጊዜ እን​ዲህ አደ​ረ​ገ​ልኝ።” በስ​ድ​ስ​ተ​ኛ​ውም ወር መል​አኩ ገብ​ር​ኤል ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ስሟ ናዝ​ሬት ወደ​ም​ት​ባ​ለው ወደ አን​ዲት የገ​ሊላ ከተማ ከዳ​ዊት ወገን ለሚ​ሆን ዮሴፍ ለሚ​ባል ሰው ወደ ታጨ​ችው ወደ አን​ዲት ድን​ግል ተላከ፤ የዚ​ያ​ችም ድን​ግል ስምዋ ማር​ያም ይባል ነበረ። መል​አ​ኩም ወደ እር​ስዋ ገብቶ፥ “ደስ ያለሽ፥ ጸጋ​ንም የተ​መ​ላሽ ሆይ፥ ደስ ይበ​ልሽ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴ​ቶች ተለ​ይ​ተሽ አንቺ የተ​ባ​ረ​ክሽ ነሽ” አላት። እር​ስ​ዋም በአ​የ​ችው ጊዜ ከአ​ነ​ጋ​ገሩ የተ​ነሣ ደነ​ገ​ጠ​ችና “ይህ እን​ዴት ያለ ሰላ​ምታ ነው?” ብላ ዐሰ​በች። መል​አ​ኩም እን​ዲህ አላት፥ “ማር​ያም ሆይ፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ባለ​ሟ​ል​ነ​ትን አግ​ኝ​ተ​ሻ​ልና አት​ፍሪ።

ሉቃስ 1:8-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ። ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። በርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን ዐውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤ እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር። ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በቀር መናገር ባለመቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ። ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ዐምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤ እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች። በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋራ ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ።

ሉቃስ 1:8-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። ዘካርያስም መልአኩን፦ እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው። መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር። በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ። የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፦ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች። በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።

ሉቃስ 1:8-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ የዘካርያስ የክህነት ቡድን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተረኛ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የክህነቱን አገልግሎት በመፈጸም ላይ ነበር። እንደ ካህናት አሠራር ልማድ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዕጣን በሚታጠንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ በውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታ መልአክ ዕጣን በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ለዘካርያስ ታየው። ዘካርያስ መልአኩን ባየው ጊዜ ደንግጦ በፍርሃት ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። የእርሱ መወለድ ለአንተ ተድላና ደስታ ይሆንልሃል፤ ብዙዎችም በመወለዱ እንዲሁ ደስ ይላቸዋል። እርሱ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ሌላም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገና በእናቱ ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል። እርሱ ከእስራኤል ሕዝብ ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ በመንፈስና በኀይል ሆኖ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፥ የማይታዘዙትንም ሰዎች ልብ ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልሳል፤ ሕዝቡንም በማንቃት ለጌታ እንዲዘጋጅ ያደርጋል።” ዘካርያስ ግን መልአኩን “ይህ ነገር እርግጥ መሆኑን በምን ዐውቃለሁ? እኔ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለች” አለው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን የምሥራች እንድነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጥቻለሁ። አንተ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚፈጸመውን ቃሌን አላመንክም፤ ስለዚህ ይህ የነገርኩህ ሁሉ እስከሚፈጸም ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ዘካርያስን ይጠባበቁ ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ስለ ዘገየባቸውም ተገረሙ። ዘካርያስ ከቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ከሰዎቹ ጋር መነጋገር አልቻለም፤ ስለዚህ እነርሱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ራእይ የታየው መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ በእጁ እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በዚህም ሁኔታ ዱዳ ሆኖ ቈየ። የአገልግሎቱም ጊዜ ከተፈጸመ በኋላ ዘካርያስ ወደ ቤቱ ሄደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወር በቤትዋ ውስጥ ተሸሽጋ ቈየች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ ይህን መልካም ነገር አደረገልኝ፤ በሰዎች መካከል የነበረብኝን ነቀፌታ አስወገደልኝ።” ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል በገሊላ ምድር ወደምትገኝ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ከእግዚአብሔር ተላከ። የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ወደ እርስዋ መጥቶ፦ “አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ [አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ]” አላት። እርስዋም በመልአኩ አነጋገር በጣም ደንግጣ፥ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤

ሉቃስ 1:8-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጀን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቶ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለችና ይህንን በምን አውቃለሁ?” አለው። መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድነግርህም ይህችንም የምሥራች እንዳበሥርህ ተልኬአለሁ፤ እነሆም፥ በጊዜያቸው የሚፈጸሙትን ቃሎቼን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆንበት ቀን ድረስ አንደበትህ ይታሰራል፤ መናገርም አትችልም፤” አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመዘግየቱም ተገረሙ። በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ፤ እርሱም በምልክት ያናግራቸው ነበር፤ ዲዳም ሆኖ ቆየ። የአገልግሎቱም ጊዜ እንደ ተፈጸመ ወደ ቤቱ ሄደ። ከነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወር ተደበቀች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ እኔን በተመለከተበት ጊዜ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል አስወገደልኝ።” በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል በገሊላ ወደምትገኝ ከተማ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።፥ የተላከውም ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ገብቶ፦ “ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤” አላት። እርሷም በንግግሩ በጣም ደንግጣ፥ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ።