ሉቃስ 1:68-79
ሉቃስ 1:68-79 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን በነቢያት አፍ እንደ ተናገረ። ከጠላቶቻችን እጅ፥ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ያስብ ዘንድ። ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሀት፥ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ በዘመናችን ሁሉ እንድናመልከው ይሰጠን ዘንድ። አንተም ሕፃን፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ትጠርግ ዘንድ በፊቱ ትሄዳለህና። ኀጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ መድኀኒታቸውን እንዲያውቁ ለአሕዛብ ትሰጣቸው ዘንድ። ከአርያም በጐበኘን በአምላካችን በይቅርታውና በቸርነቱ። በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩት ብርሃኑን ያሳያቸው ዘንድ፥ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።”
ሉቃስ 1:68-79 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤ መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷልና። በባሪያው በዳዊት ቤት፣ የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤ ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤ ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣ በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው። “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤ የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣ ከአምላካችንም በጎ ምሕረት የተነሣ፣ የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤ ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።”
ሉቃስ 1:68-79 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።
ሉቃስ 1:68-79 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ሕዝቡን በምሕረት ስለ ጐበኘና ስላዳነ፥ የእስራኤል አምላክ፥ ጌታ ይመስገን! ከአገልጋዩ ከዳዊት ዘር ኀያል አዳኝ አስነሥቶልናል፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ከጠላቶቻችንና ከባላጋራዎቻችን እጅ አድኖናል፤ ይህንንም ማድረጉ ለአባቶቻችን ምሕረትን እንደሚያደርግና የተናገረውንም ቅዱስ ቃል ኪዳኑን እንደሚፈጽም በማሰብ ነው። ይህንንም ቃል ኪዳን፥ በመሐላ የሰጠው ለአባታችን ለአብርሃም ነበር፤ የተስፋውም ቃል ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ወጥተን፥ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው ነው፤ እንዲሁም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስናና በጽድቅ መኖር እንድንችል ነው። ደግሞም አንተ ሕፃን፥ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ። መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በጌታ ፊት ትሄዳለህ። ጌታም ኃጢአታቸውን ይቅር በማለት የመዳንን ዕውቀት ይሰጣቸዋል። አምላካችን መሓሪና ርኅሩኅ በመሆኑ የደኅንነት ብርሃን ከወደላይ እንዲበራልን ያደርጋል። እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ላሉት ሁሉ ያበራል፤ እርምጃችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”
ሉቃስ 1:68-79 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፥ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንዲሁም ለአባቶቻችን ምሕረትን አደረገ፤ ቅዱስ ኪዳኑንም ለአባታችን ለአብርሃም በመሐላ እንደማለለት አስታወሰ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሃት በዘመናችን ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንዲሁም በኀጢአታቸው ስርየት የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ በአምላካችን የርኅራኄ ምሕረት ከላይ የሚመጣው ብርሃን ይጐበኘናልና፤ እርሱም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”