ሉቃስ 1:57-66
ሉቃስ 1:57-66 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የኤልሣቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ዘመዶችዋና ጎረቤቶችዋም እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። ከዚህም በኋላ በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገዝሩት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን መልሳ፥ “አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ” አለች። እነርሱም፥ “ከዘመዶችሽ ስሙ እንደዚህ የሚባል የለም” አሉአት። አባቱንም ጠቅሰው፥ “ማን ሊሉት ትወዳለህ?” አሉት። ብራናም ለመነና “ስሙ ዮሐንስ ይባል” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ። በዚያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍርሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይሁዳ በተራራማው ሀገር ሁሉ ተወራ። የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና።
ሉቃስ 1:57-66 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች። እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ። ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ። ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ። ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከእርሱ ጋር ነበርና።
ሉቃስ 1:57-66 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ። እናቱ ግን መልሳ፦ አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ አለች። እነርሱም፦ ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም አሉአት። አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት። ብራናም ለምኖ፦ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ። ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፦ እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን? እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና።
ሉቃስ 1:57-66 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ሁሉ ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ተደሰቱ። ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛው ቀን፥ በግዝረቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ተሰብስበው መጡ፤ ባባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር፤ እናቱ ግን “እንዲህ አይሆንም፤ ስሙ ዮሐንስ ነው” አለች። እነርሱም “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም?” አሉአት። ከዚህም በኋላ አባቱን፦ “ልጅህ ማን ተብሎ እንዲጠራ ትፈልጋለህ?” ብለው በምልክት ጠየቁት። ዘካርያስም መጻፊያ እንዲሰጡት ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በዚህ ነገር ተደነቁ። በዚያኑ ጊዜ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈቶለት መናገር ቻለ፤ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። ከዚህም የተነሣ በጐረቤቶቻቸው ሁሉ ፍርሀት አደረባቸው፤ ዜናውም በተራራማው በይሁዳ ምድር ሁሉ ተሰማ። ይህን ነገር የሰሙ ሁሉ፥ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ይህም የሆነው የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ነው።
ሉቃስ 1:57-66 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርሷ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። እናቱ ግን መልሳ፦ “እንዲህ አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ እንጂ፤” አለች። እነርሱም፦ “ከዘመዶችሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፤” አሉአት። ማን ተብሎ ቢጠራ እንደሚወድ አባቱንም በምልክት ጠየቁ። ሰሌዳም ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፤” ብሎ ጻፈ። ሁሉም ተደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ተናገረ። በጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በተራራማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ በእርግጥ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና።