የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 1:5-80

ሉቃስ 1:5-80 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በይ​ሁዳ ንጉሥ በሄ​ሮ​ድስ ዘመን ከአ​ብያ ክፍል የሆነ ዘካ​ር​ያስ የሚ​ባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስ​ቱም ከአ​ሮን ልጆች ወገን ነበ​ረች፤ ስም​ዋም ኤል​ሳ​ቤጥ ነበረ። ሁለ​ቱም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ጻድ​ቃን ነበሩ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥር​ዐ​ትና በት​እ​ዛ​ዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚ​ሄዱ ነበሩ። ልጅም አል​ነ​በ​ራ​ቸ​ውም፤ ኤል​ሳ​ቤጥ መካን ነበ​ረ​ችና፤ ሁለ​ቱም አር​ጅ​ተው ነበር፤ ዘመ​ና​ቸ​ውም አልፎ ነበር። እር​ሱም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በተ​ራው የክ​ህ​ነ​ትን ሥራ በሚ​ሠ​ራ​በት ጊዜ፥ ካህ​ናት እን​ደ​ሚ​ያ​ደ​ር​ጉት የሚ​ያ​ጥ​ን​በት ጊዜ ደረሰ፤ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤተ መቅ​ደ​ስም ገባ። ዕጣን በሚ​ያ​ጥ​ን​በት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸ​ልዩ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አ​ክም በዕ​ጣን መሠ​ው​ያው በስ​ተ​ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካ​ር​ያ​ስም ባየው ጊዜ ደነ​ገጠ፤ ፍር​ሀ​ትም ረዓ​ድም ወረ​ደ​በት። መል​አ​ኩም እን​ዲህ አለው፥ “ዘካ​ር​ያስ ሆይ፥ አት​ፍራ፤ ጸሎ​ትህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ተሰ​ም​ቶ​አ​ልና፤ ሚስ​ትህ ኤል​ሣ​ቤ​ጥም ትፀ​ን​ሳ​ለች፤ ወንድ ልጅ​ንም ትወ​ል​ድ​ል​ሃ​ለች፤ ስሙ​ንም ዮሐ​ንስ ትለ​ዋ​ለህ። ደስ​ታና ሐሤ​ትም ይሆ​ን​ል​ሃል፤ በመ​ወ​ለ​ዱም ብዙ​ዎች ደስ ይላ​ቸ​ዋል። እርሱ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ታላቅ ይሆ​ና​ልና የወ​ይን ጠጅና የሚ​ያ​ሰ​ክ​ርም መጠጥ ሁሉ አይ​ጠ​ጣም፤ ከእ​ናቱ ማሕ​ፀን ጀም​ሮም መን​ፈስ ቅዱስ ይመ​ላ​በ​ታል። ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ብዙ​ዎ​ችን ወደ አም​ላ​ካ​ቸው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ል​ሳ​ቸ​ዋል። እር​ሱም የአ​ባ​ቶ​ችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከ​ሓ​ድ​ያ​ን​ንም ዐሳብ ወደ ጻድ​ቃን ዕው​ቀት ይመ​ልስ ዘንድ፥ ሕዝ​ብ​ንም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ዘ​ጋጀ ያደ​ርግ ዘንድ በኤ​ል​ያስ መን​ፈ​ስና ኀይል በፊቱ ይሄ​ዳል።” ዘካ​ር​ያ​ስም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ እን​ዲህ አለው፥ “ይህ እን​ደ​ሚ​ሆን በምን አው​ቃ​ለሁ? እነሆ፥ እኔ አር​ጅ​ች​አ​ለሁ፤ የሚ​ስ​ቴም ዘመ​ንዋ አል​ፏል።” መል​አ​ኩም መልሶ እን​ዲህ አለው፥ “እኔ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት የም​ቆ​መው ገብ​ር​ኤል ነኝ፤ ይህ​ንም እነ​ግ​ር​ህና አበ​ሥ​ርህ ዘንድ ወደ አንተ ተል​ኬ​አ​ለሁ። አሁ​ንም በጊ​ዜው የሚ​ሆ​ነ​ው​ንና የሚ​ፈ​ጸ​መ​ውን ነገ​ሬን አላ​መ​ን​ኽ​ኝ​ምና ይህ እስ​ኪ​ሆን ድረስ ዲዳ ትሆ​ና​ለህ፤ መና​ገ​ርም ይሳ​ን​ሃል።” ሕዝቡ ግን ዘካ​ር​ያ​ስን ይጠ​ብ​ቁት ነበር፤ በቤተ መቅ​ደስ ውስጥ ዘግ​ይቶ ነበ​ርና እጅግ ተደ​ነቁ። ወደ እነ​ርሱ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜም እነ​ር​ሱን ማነ​ጋ​ገር ተሳ​ነው፤ በቤተ መቅ​ደ​ስም የተ​ገ​ለ​ጠ​ለት እን​ዳለ ዐወቁ፤ እን​ዲ​ሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያ​መ​ለ​ከ​ታ​ቸው ኖረ። ከዚ​ህም በኋላ የማ​ገ​ል​ገሉ ወራት በተ​ፈ​ጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ። ከእ​ነ​ዚ​ያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤል​ሳ​ቤጥ ፀነ​ሰች፤ ፅን​ስ​ዋ​ንም ለአ​ም​ስት ወር ሸሸ​ገች፤ እን​ዲህ ስትል፦ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድ​ቤን ያርቅ ዘንድ በጐ​በ​ኘኝ ጊዜ እን​ዲህ አደ​ረ​ገ​ልኝ።” በስ​ድ​ስ​ተ​ኛ​ውም ወር መል​አኩ ገብ​ር​ኤል ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ስሟ ናዝ​ሬት ወደ​ም​ት​ባ​ለው ወደ አን​ዲት የገ​ሊላ ከተማ ከዳ​ዊት ወገን ለሚ​ሆን ዮሴፍ ለሚ​ባል ሰው ወደ ታጨ​ችው ወደ አን​ዲት ድን​ግል ተላከ፤ የዚ​ያ​ችም ድን​ግል ስምዋ ማር​ያም ይባል ነበረ። መል​አ​ኩም ወደ እር​ስዋ ገብቶ፥ “ደስ ያለሽ፥ ጸጋ​ንም የተ​መ​ላሽ ሆይ፥ ደስ ይበ​ልሽ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴ​ቶች ተለ​ይ​ተሽ አንቺ የተ​ባ​ረ​ክሽ ነሽ” አላት። እር​ስ​ዋም በአ​የ​ችው ጊዜ ከአ​ነ​ጋ​ገሩ የተ​ነሣ ደነ​ገ​ጠ​ችና “ይህ እን​ዴት ያለ ሰላ​ምታ ነው?” ብላ ዐሰ​በች። መል​አ​ኩም እን​ዲህ አላት፥ “ማር​ያም ሆይ፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ባለ​ሟ​ል​ነ​ትን አግ​ኝ​ተ​ሻ​ልና አት​ፍሪ። እነሆ፥ ትፀ​ን​ሻ​ለሽ፤ ወንድ ልጅ​ንም ትወ​ል​ጃ​ለሽ፤ ስሙ​ንም ኢየ​ሱስ ትይ​ዋ​ለሽ። እር​ሱም ታላቅ ነው፤ የል​ዑል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅም ይባ​ላል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ክም የአ​ባ​ቱን የዳ​ዊ​ትን ዙፋን ይሰ​ጠ​ዋል። ለያ​ዕ​ቆብ ወገ​ንም ለዘ​ለ​ዓ​ለሙ ይነ​ግ​ሣል፤ ለመ​ን​ግ​ሥ​ቱም ፍጻሜ የለ​ውም።” ማር​ያ​ምም መል​አ​ኩን፥ “ወንድ ስለ​ማ​ላ​ውቅ ይህ እን​ዴት ይሆ​ን​ል​ኛል?” አለ​ችው። መል​አ​ኩም መልሶ እን​ዲህ አላት፥ “መን​ፈስ ቅዱስ ያድ​ር​ብ​ሻል፤ የል​ዑል ኀይ​ልም ይጋ​ር​ድ​ሻል፤ ከአ​ንቺ የሚ​ወ​ለ​ደ​ውም ቅዱስ ነው፤ የል​ዑል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅም ይባ​ላል። እነሆ፥ ከዘ​መ​ዶ​ችሽ ወገን የም​ት​ሆን ኤል​ሣ​ቤ​ጥም እር​ስዋ እንኳ በእ​ር​ጅ​ናዋ ወንድ ልጅን ፀን​ሳ​ለች፤ መካን ትባል የነ​በ​ረ​ችው ከፀ​ነ​ሰች እነሆ፥ ይህ ስድ​ስ​ተኛ ወር ነው። ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሚ​ሳ​ነው ነገር የለ​ምና”። ማር​ያ​ምም መል​አ​ኩን፥ “እነ​ሆኝ፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ባሪ​ያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁ​ን​ልኝ” አለ​ችው፤ ከዚህ በኋ​ላም መል​አኩ ከእ​ር​ስዋ ዘንድ ሄደ። በዚ​ያም ወራት ማር​ያም ፈጥና ተነ​ሣች፤ ወደ ተራ​ራ​ማው ሀገር ወደ ይሁዳ ከተ​ማም ደረ​ሰች። ወደ ዘካ​ር​ያስ ቤትም ገብታ ለኤ​ል​ሣ​ቤጥ ሰላ​ምታ ሰጠ​ቻት። ኤል​ሳ​ቤ​ጥም የማ​ር​ያ​ምን ሰላ​ምታ በሰ​ማች ጊዜ ፅንሱ በማ​ኅ​ፀ​ንዋ ዘለለ፤ በኤ​ል​ሣ​ቤ​ጥም መን​ፈስ ቅዱስ መላ​ባት። በታ​ላቅ ቃልም ጮሃ እን​ዲህ አለች፥ “ከሴ​ቶች ተለ​ይ​ተሽ አንቺ የተ​ባ​ረ​ክሽ ነሽ፤ የማ​ኅ​ፀ​ን​ሽም ፍሬ ቡሩክ ነው። የጌ​ታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምን​ድን ነኝ? እነሆ፥ ሰላ​ምታ ስት​ሰ​ጭኝ ቃል​ሽን በሰ​ማሁ ጊዜ፥ ፅንሱ በማ​ኅ​ፀኔ በደ​ስታ ዘሎ​አ​ልና። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የነ​ገ​ሩሽ ቃል እን​ደ​ሚ​ሆን የም​ታ​ምኚ አንቺ ብፅ​ዕት ነሽ።” ማር​ያ​ምም እን​ዲህ አለች፥ “ሰው​ነቴ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታከ​ብ​ረ​ዋ​ለች። ልቡ​ና​ዬም በአ​ም​ላኬ በመ​ድ​ኀ​ኒቴ ሐሤት ታደ​ር​ጋ​ለች። የባ​ር​ያ​ውን ትሕ​ትና ተመ​ል​ክ​ቶ​አ​ልና። እነሆ፥ ከዛሬ ጀምሮ ትው​ልድ ሁሉ ብፅ​ዕት ይሉ​ኛል። ታላቅ ሥራን ሠር​ቶ​ል​ኛ​ልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ይቅ​ር​ታ​ውም ለሚ​ፈ​ሩት ለልጅ ልጅ ነው። በክ​ንዱ ኀይ​ልን አደ​ረገ፤ በል​ባ​ቸው ዐሳብ የሚ​ታ​በ​ዩ​ት​ንም በተ​ና​ቸው። ኀያ​ላ​ኑን ከዙ​ፋ​ና​ቸው አዋ​ረ​ዳ​ቸው፤ ትሑ​ታ​ኑ​ንም ከፍ ከፍ አደ​ረ​ጋ​ቸው። የተ​ራ​ቡ​ትን ከበ​ረ​ከቱ አጠ​ገ​ባ​ቸው፤ ባለ​ጠ​ጎ​ች​ንም ባዶ እጃ​ቸ​ውን ሰደ​ዳ​ቸው። ብላ​ቴ​ና​ውን እስ​ራ​ኤ​ልን ተቀ​በ​ለው፤ ይቅ​ር​ታ​ው​ንም ዐሰበ። ለአ​ባ​ቶ​ቻ​ችን ለአ​ብ​ር​ሃ​ምና ለዘሩ እስከ ዘለ​ዓ​ለም እንደ ተና​ገ​ረው።” ማር​ያ​ምም ሦስት ወር ያህል በእ​ር​ስዋ ዘንድ ተቀ​መ​ጠች፤ ከዚህ በኋ​ላም ወደ ቤቷ ተመ​ለ​ሰች። የኤ​ል​ሣ​ቤ​ጥም የመ​ው​ለ​ጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለ​ደች። ዘመ​ዶ​ች​ዋና ጎረ​ቤ​ቶ​ች​ዋም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቸር​ነ​ቱን እን​ዳ​በ​ዛ​ላት በሰሙ ጊዜ ከእ​ር​ስዋ ጋር ደስ አላ​ቸው። ከዚ​ህም በኋላ በስ​ም​ን​ተ​ኛው ቀን ሕፃ​ኑን ሊገ​ዝ​ሩት መጡ፤ በአ​ባ​ቱም ስም ዘካ​ር​ያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን መልሳ፥ “አይ​ሆ​ንም፥ ዮሐ​ንስ ይባል እንጂ” አለች። እነ​ር​ሱም፥ “ከዘ​መ​ዶ​ችሽ ስሙ እን​ደ​ዚህ የሚ​ባል የለም” አሉ​አት። አባ​ቱ​ንም ጠቅ​ሰው፥ “ማን ሊሉት ትወ​ዳ​ለህ?” አሉት። ብራ​ናም ለመ​ነና “ስሙ ዮሐ​ንስ ይባል” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደ​ነቁ። ያን​ጊ​ዜም አፉ ተከ​ፈተ፤ አን​ደ​በ​ቱም ተና​ገረ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አመ​ሰ​ገነ። በዚ​ያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍር​ሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይ​ሁዳ በተ​ራ​ራ​ማው ሀገር ሁሉ ተወራ። የሰ​ሙ​ትም ሁሉ፥ “እን​ግ​ዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በል​ባ​ቸው አኖ​ሩት፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እጅ በእ​ርሱ ላይ ነበ​ረ​ችና። በአ​ባቱ በዘ​ካ​ር​ያ​ስም መን​ፈስ ቅዱስ መላ​በት፤ እን​ዲ​ህም ብሎ ትን​ቢት ተና​ገረ፦ “ይቅር ያለን፥ ለወ​ገ​ኖ​ቹም ድኅ​ነ​ትን ያደ​ረገ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ስ​ገን፤ ከባ​ር​ያው ከዳ​ዊት ቤት የም​ን​ድ​ን​በ​ትን ቀንድ አስ​ነ​ሣ​ልን፤ ከጥ​ንት ጀምሮ በነ​በሩ በቅ​ዱ​ሳን በነ​ቢ​ያት አፍ እንደ ተና​ገረ። ከጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችን እጅ፥ ከሚ​ጠ​ሉ​ንም ሁሉ እጅ ያድ​ነን ዘንድ። ቸር​ነ​ቱን ከአ​ባ​ቶ​ቻ​ችን ጋር ያደ​ርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳ​ኑ​ንም ያስብ ዘንድ። ለአ​ባ​ታ​ችን ለአ​ብ​ር​ሃም የማ​ለ​ውን መሐላ ያስብ ዘንድ። ከጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችን እጅ ድነን ያለ ፍር​ሀት፥ በቅ​ድ​ስ​ናና በጽ​ድቅ በፊቱ በዘ​መ​ና​ችን ሁሉ እን​ድ​ና​መ​ል​ከው ይሰ​ጠን ዘንድ። አን​ተም ሕፃን፥ የል​ዑል ነቢይ ትባ​ላ​ለህ፤ መን​ገ​ዱን ትጠ​ርግ ዘንድ በፊቱ ትሄ​ዳ​ለ​ህና። ኀጢ​አ​ታ​ቸው ይሰ​ረ​ይ​ላ​ቸው ዘንድ መድ​ኀ​ኒ​ታ​ቸ​ውን እን​ዲ​ያ​ውቁ ለአ​ሕ​ዛብ ትሰ​ጣ​ቸው ዘንድ። ከአ​ር​ያም በጐ​በ​ኘን በአ​ም​ላ​ካ​ችን በይ​ቅ​ር​ታ​ውና በቸ​ር​ነቱ። በጨ​ለ​ማና በሞት ጥላ ለነ​በ​ሩት ብር​ሃ​ኑን ያሳ​ያ​ቸው ዘንድ፥ እግ​ሮ​ቻ​ች​ን​ንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።” ሕፃ​ኑም አደገ፤ በመ​ን​ፈስ ቅዱ​ስም ጸና፤ ለእ​ስ​ራ​ኤ​ልም እስ​ከ​ታ​የ​በት ቀን ድረስ በም​ድረ በዳ ኖረ።

ሉቃስ 1:5-80 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ነገድ ስትሆን፣ ስሟም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ። አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ። ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። በርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን ዐውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤ እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር። ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በቀር መናገር ባለመቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ። ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ዐምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤ እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች። በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋራ ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።” ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ። ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ ብፅዕት ናት!” ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሠኛለች፤ እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ምስጉን ይሉኛል፤ ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤ በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤ ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰድዷቸዋል፤ ምሕረቱን በማስታወስ፣ ብላቴናውን እስራኤልን ረድቷል፤ ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች። እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ። ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ። ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ። ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከርሱ ጋራ ነበርና። የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤ መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷልና። በብላቴናው በዳዊት ቤት፣ የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤ ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤ ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣ በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው። “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤ የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣ ከአምላካችንም ጥልቅ ምሕረት የተነሣ፣ የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤ ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።” ሕፃኑም እያደገ፣ በመንፈስም እየጠነከረ ሄደ፤ ለእስራኤልም ሕዝብ በይፋ እስከ ታየበት ቀን ድረስ በበረሓ ኖረ።

ሉቃስ 1:5-80 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። ዘካርያስም መልአኩን፦ እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው። መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር። በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ። የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፦ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች። በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን፦ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። ማርያምም እንዲህ አለች፦ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል። ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ። እናቱ ግን መልሳ፦ አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ አለች። እነርሱም፦ ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም አሉአት። አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት። ብራናም ለምኖ፦ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ። ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፦ እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን? እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ፦ የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።

ሉቃስ 1:5-80 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሄሮድስ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረበት ዘመን፥ ከአብያ የክህነት አገልግሎት ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል ካህን ነበር። እርሱም ከአሮን ዘር የምትወለድ ኤልሳቤጥ የምትባል ሚስት ነበረችው። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የጌታንም ትእዛዝና ሥርዓት ያለ ነቀፋ ይጠብቁ ነበር። ኤልሳቤጥ መኻን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ደግሞ ሁለቱም በጣም አርጅተው ነበር። በዚያን ጊዜ የዘካርያስ የክህነት ቡድን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተረኛ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የክህነቱን አገልግሎት በመፈጸም ላይ ነበር። እንደ ካህናት አሠራር ልማድ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዕጣን በሚታጠንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ በውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታ መልአክ ዕጣን በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ለዘካርያስ ታየው። ዘካርያስ መልአኩን ባየው ጊዜ ደንግጦ በፍርሃት ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። የእርሱ መወለድ ለአንተ ተድላና ደስታ ይሆንልሃል፤ ብዙዎችም በመወለዱ እንዲሁ ደስ ይላቸዋል። እርሱ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ሌላም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገና በእናቱ ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል። እርሱ ከእስራኤል ሕዝብ ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ በመንፈስና በኀይል ሆኖ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፥ የማይታዘዙትንም ሰዎች ልብ ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልሳል፤ ሕዝቡንም በማንቃት ለጌታ እንዲዘጋጅ ያደርጋል።” ዘካርያስ ግን መልአኩን “ይህ ነገር እርግጥ መሆኑን በምን ዐውቃለሁ? እኔ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለች” አለው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን የምሥራች እንድነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጥቻለሁ። አንተ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚፈጸመውን ቃሌን አላመንክም፤ ስለዚህ ይህ የነገርኩህ ሁሉ እስከሚፈጸም ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ዘካርያስን ይጠባበቁ ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ስለ ዘገየባቸውም ተገረሙ። ዘካርያስ ከቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ከሰዎቹ ጋር መነጋገር አልቻለም፤ ስለዚህ እነርሱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ራእይ የታየው መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ በእጁ እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በዚህም ሁኔታ ዱዳ ሆኖ ቈየ። የአገልግሎቱም ጊዜ ከተፈጸመ በኋላ ዘካርያስ ወደ ቤቱ ሄደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወር በቤትዋ ውስጥ ተሸሽጋ ቈየች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ ይህን መልካም ነገር አደረገልኝ፤ በሰዎች መካከል የነበረብኝን ነቀፌታ አስወገደልኝ።” ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል በገሊላ ምድር ወደምትገኝ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ከእግዚአብሔር ተላከ። የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ወደ እርስዋ መጥቶ፦ “አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ [አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ]” አላት። እርስዋም በመልአኩ አነጋገር በጣም ደንግጣ፥ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤ እነሆ! ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። በእስራኤልም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” ማርያም መልአኩን “እኔ ድንግል ነኝ፤ ታዲያ፥ ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል እግዚአብሔርም ኀይል በአንቺ ላይ ይሆናል፤ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ሕፃን ቅዱስ ነው፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ይባላል። ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እንኳ መኻን ስትባል ኖራ አሁን በስተእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ ከፀነሰችም እነሆ፥ ስድስተኛ ወርዋ ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም።” ከዚያም በኋላ ማርያም፥ “እነሆ! እኔ የጌታ አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ መልአኩ ተለይቶአት ሄደ። በዚያን ጊዜ ማርያም በተራራማው በይሁዳ አገር ወዳለችው ከተማ በፍጥነት ተነሥታ ሄደች። ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥ የማርያምን የሰላምታ ቃል በሰማች ጊዜ በማሕፀንዋ የነበረው ሕፃን ዘለለ። ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ ከአንቺ የሚወለደውም የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ልትጐበኘኝ መምጣትዋ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው፤ ገና የሰላምታሽን ድምፅ ከመስማቴ በማሕፀኔ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ። አንቺ ጌታ የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የተባረክሽ ነሽ!” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታመሰግናለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤ እግዚአብሔር እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቶአልና፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ የተባረክሽ ነሽ ይሉኛል፤ ኀያሉ እግዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልኛልና። ስሙም ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል። በብርቱ ክንዱ ኀይሉን አሳይቶአል፤ ትዕቢተኞችንም ከነሐሳባቸው በትኖአቸዋል። ታላላቅ ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ዝቅተኞችን ግን በክብር ከፍ አድርጎአቸዋል። የተራቡትን በመልካም ነገር አጥግቦአቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዶ እጃቸውን ሰዶአቸዋል፤ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም ያሳየውን ምሕረት በማስታወስ፥ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቶታል። ይህንንም ያደረገው ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ነው።” ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያኽል ከቈየች በኋላ ወደ ቤትዋ ተመልሳ ሄደች። ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ሁሉ ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ተደሰቱ። ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛው ቀን፥ በግዝረቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ተሰብስበው መጡ፤ ባባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር፤ እናቱ ግን “እንዲህ አይሆንም፤ ስሙ ዮሐንስ ነው” አለች። እነርሱም “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም?” አሉአት። ከዚህም በኋላ አባቱን፦ “ልጅህ ማን ተብሎ እንዲጠራ ትፈልጋለህ?” ብለው በምልክት ጠየቁት። ዘካርያስም መጻፊያ እንዲሰጡት ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በዚህ ነገር ተደነቁ። በዚያኑ ጊዜ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈቶለት መናገር ቻለ፤ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። ከዚህም የተነሣ በጐረቤቶቻቸው ሁሉ ፍርሀት አደረባቸው፤ ዜናውም በተራራማው በይሁዳ ምድር ሁሉ ተሰማ። ይህን ነገር የሰሙ ሁሉ፥ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ይህም የሆነው የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ነው። የሕፃኑ አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦ “ሕዝቡን በምሕረት ስለ ጐበኘና ስላዳነ፥ የእስራኤል አምላክ፥ ጌታ ይመስገን! ከአገልጋዩ ከዳዊት ዘር ኀያል አዳኝ አስነሥቶልናል፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ከጠላቶቻችንና ከባላጋራዎቻችን እጅ አድኖናል፤ ይህንንም ማድረጉ ለአባቶቻችን ምሕረትን እንደሚያደርግና የተናገረውንም ቅዱስ ቃል ኪዳኑን እንደሚፈጽም በማሰብ ነው። ይህንንም ቃል ኪዳን፥ በመሐላ የሰጠው ለአባታችን ለአብርሃም ነበር፤ የተስፋውም ቃል ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ወጥተን፥ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው ነው፤ እንዲሁም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስናና በጽድቅ መኖር እንድንችል ነው። ደግሞም አንተ ሕፃን፥ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ። መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በጌታ ፊት ትሄዳለህ። ጌታም ኃጢአታቸውን ይቅር በማለት የመዳንን ዕውቀት ይሰጣቸዋል። አምላካችን መሓሪና ርኅሩኅ በመሆኑ የደኅንነት ብርሃን ከወደላይ እንዲበራልን ያደርጋል። እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ላሉት ሁሉ ያበራል፤ እርምጃችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እስከ ታየበት ጊዜ ድረስ በበረሓ ኖረ።

ሉቃስ 1:5-80 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ሴት ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ ይመላለሱ ነበር። ኤልሳቤጥም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጀን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቶ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለችና ይህንን በምን አውቃለሁ?” አለው። መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድነግርህም ይህችንም የምሥራች እንዳበሥርህ ተልኬአለሁ፤ እነሆም፥ በጊዜያቸው የሚፈጸሙትን ቃሎቼን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆንበት ቀን ድረስ አንደበትህ ይታሰራል፤ መናገርም አትችልም፤” አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመዘግየቱም ተገረሙ። በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ፤ እርሱም በምልክት ያናግራቸው ነበር፤ ዲዳም ሆኖ ቆየ። የአገልግሎቱም ጊዜ እንደ ተፈጸመ ወደ ቤቱ ሄደ። ከነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወር ተደበቀች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ እኔን በተመለከተበት ጊዜ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል አስወገደልኝ።” በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል በገሊላ ወደምትገኝ ከተማ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።፥ የተላከውም ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ገብቶ፦ “ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤” አላት። እርሷም በንግግሩ በጣም ደንግጣ፥ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፦ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርሷ ደግሞ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን ትባል ለነበረችው ለእርሷም ይህ ስድስተኛ ወሯ ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው አንዳች ነገር የለምና።” ማርያምም፦ “እነሆኝ የጌታ አገልጋይ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፤” አለች። መልአኩም ከእርሷ ተለይቶ ሄደ። ማርያምም በእነዚያ ቀናት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር በይሁዳ ወደምትገኝ ከተማ ፈጥና ሄደች፤ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል። በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤ በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። እስራኤልን አገልጋዩን፥ ምሕረቱን በማስታወስ፥ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም እንደ ተናገረው ረድቶአል።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚያም ወደ ቤትዋ ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርሷ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። እናቱ ግን መልሳ፦ “እንዲህ አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ እንጂ፤” አለች። እነርሱም፦ “ከዘመዶችሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፤” አሉአት። ማን ተብሎ ቢጠራ እንደሚወድ አባቱንም በምልክት ጠየቁ። ሰሌዳም ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፤” ብሎ ጻፈ። ሁሉም ተደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ተናገረ። በጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በተራራማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ በእርግጥ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢት ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፥ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንዲሁም ለአባቶቻችን ምሕረትን አደረገ፤ ቅዱስ ኪዳኑንም ለአባታችን ለአብርሃም በመሐላ እንደማለለት አስታወሰ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሃት በዘመናችን ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንዲሁም በኀጢአታቸው ስርየት የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ በአምላካችን የርኅራኄ ምሕረት ከላይ የሚመጣው ብርሃን ይጐበኘናልና፤ እርሱም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።