ሰቈቃወ 4:1-22
ሰቈቃወ 4:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ብር እንዴት ተለወጠ! የከበረው ዕንቍ በጎዳናው ሁሉ እንዴት ተበተነ! ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ! ጋሜል። አራዊት እንኳ ጡታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ሴት ልጆች ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኞች ሆኑ። ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፤ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፤ የሚቈርስላቸውም የለም። ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፤ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ። ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች፥ ከሰዶም ኀጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኀጢአት በዛች። ዛይ። ቅዱሳኖችዋ ከበረድ ይልቅ ነጡ፤ ከወተትም ይልቅ ነጡ፤ በመውጣታቸውም ሰንፔር ከሚባል ዕንቍ ይልቅ ፈጽመው ቀሉ። ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፤ በመንገድም አልታወቁም፤ ቍርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፤ ደርቆአል፤ እንደ እንጨትም ሆኖአል። ጤት። በሰይፍ የሞቱት በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ዐልፈዋል። ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻቸውን ቀቅለዋል፤ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኖአቸው። ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፤ ጽኑ ቍጣውንም አፍስሶአል፤ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፤ መሠረቷንም በላች። ላሜድ። የምድር ነገሥታት፥ በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ፥ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንደሚገባ አላመኑም። ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ፥ ስለ ነቢያቷ ኀጢአትና ስለ ካህናቷ በደል ነው። ኖን። እነርሱ ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤ ልብሳቸውም እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል። ሳምኬት። እናንተ ከርኩሳን ራቁ፥ አስተምሩአቸው፤ ራቁ፥ ራቁ በሉአቸው፤ አትንኩአቸውም። ታውከዋልና ዳግመኛ እንዳይኖሩባት ለአሕዛብ ንገሩአቸው። ዔ። የእግዚአብሔር ፊት ክፍላቸው ነበረ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፤ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፤ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም። ፌ። በማያድን ወገን እያመንን ረዳታችን ከንቱ ስለ ሆነ፥ እኛ ገና በሕይወት ሳለን ዐይኖቻችን ጠፉ። ጻዴ። ልጆቻችንን ወደ አደባባያችን እንዳይወጡ ከለከልን፤ የምንጠፋበት ጊዜ ደርሷልና ዘመናችን አለቀ፤ የምንጠፋበትም ጊዜ ቀረበ። ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በምድረ በዳም ሸመቁብን። ሬስ። ስለ እርሱ፥ “በአሕዛብ ውስጥ በጥላው በሕይወት እንኖራለን” ያልነው፥ በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በወጥመዳቸው ተያዘ። ሣን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፥ ሐሤትም አድርጊ፤ የእግዚአብሔር ጽዋ ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋልና፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ፥ ትራቆቻለሽም። ታው። የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ በደልሽ ተፈጸመ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይጐበኘዋል፤ ኀጢአትሽንም ይገልጣል።
ሰቈቃወ 4:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወርቁ እንዴት ደበሰ! ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የከበሩ ድንጋዮች፣ በየመንገዱ ዳር ተበታትነዋል። እንደ ወርቅ ይቈጠሩ የነበሩ፣ የከበሩ የጽዮን ወንዶች ልጆች፣ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው፣ እንዴት አሁን እንደ ሸክላ ዕቃ ሆኑ! ቀበሮዎች እንኳን ግልገሎቻቸውን ለማጥባት፣ ጡታቸውን ይሰጣሉ፤ ሕዝቤ ግን በምድረ በዳ እንዳሉ ሰጎኖች፣ ጨካኞች ሆኑ። ከውሃ ጥም የተነሣ፣ የሕፃናት ምላስ ከላንቃቸው ጋር ተጣበቀ፤ ልጆቹ ምግብ ለመኑ፤ ነገር ግን ማንም አልሰጣቸውም። ምርጥ ምግብ ይበሉ የነበሩ፣ ተቸግረው በየመንገዱ ላይ ተንከራተቱ፤ ሐምራዊ ግምጃ ለብሰው ያደጉ፣ አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተኙ። በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት፣ የማንም እጅ ሳይረዳት፣ በድንገት ከተገለበጠችው፣ ሰዶም ላይ ከደረሰው ቅጣት ይልቅ ታላቅ ነው። መሳፍንታቸው ከበረዶ ይልቅ ብሩህ፣ ከወተትም ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ሰውነታቸው ከቀይ ዕንየቀላ፣ መልካቸውም እንደ ሰንፌር ነበር። አሁን ግን ከጥላሸት ይልቅ ጠቍረዋል፤ በመንገድም የሚያውቃቸው የለም፤ ቈዳቸው ከዐጥንታቸው ጋር ተጣብቋል፤ እንደ ዕንጨትም ደርቀዋል። በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣ በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤ ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣ በራብ ደርቀው ያልቃሉ። ሕዝቤ ባለቀበት ጊዜ፣ ምግብ እንዲሆኗቸው፣ ርኅሩኆቹ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው፣ ልጆቻቸውን ቀቀሉ። እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤ ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤ መሠረቷን እንዲበላ፣ በጽዮን እሳት ለኰሰ። ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣ የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣ የምድር ነገሥታት፣ ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም። ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣ ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኗል፤ በውስጧ፣ የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና። እንደ ታወሩ ሰዎች፣ በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤ ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣ በደም እጅግ ረክሰዋል። ሰዎች “ሂዱ! እናንት ርኩሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤ “ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤ ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣ በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣ “ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ። እግዚአብሔር ራሱ በትኗቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤ ካህናቱ አልተከበሩም፤ ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም። ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣ ዐይኖቻችን ደከሙ፤ ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣ ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን። ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤ ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤ መጨረሻችን ቀርቧል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤ ፍጻሜያችን መጥቷልና። ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣ ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በምድረ በዳም ሸመቁብን። በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣ በወጥመዳቸው ተያዘ፤ በጥላው ሥር፣ በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር። አንቺ በዖፅ ምድር የምትኖሪ፣ የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ ነገር ግን ለአንቺም ደግሞ ጽዋው ይደርስሻል፤ ትሰክሪያለሽ፤ ዕርቃንሽንም ትጋለጫለሽ። የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ቅጣትሽ ያበቃል፤ እርሱም የስደትሽን ዘመን አያራዝምም፤ ነገር ግን አንቺ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፤ ኀጢአትሽን ይቀጣል፤ ክፋትሽንም ይፋ ያወጣል።
ሰቈቃወ 4:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ። ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ! ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፥ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች። ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፥ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም። ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፥ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ። ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች። ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፥ ገላቸው ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ። ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፥ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፥ ደርቆአል፥ እንደ እንጨት ሆኖአል። ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፥ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል። ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፥ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኑአቸው። ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቍጣውን አፍስሶአል፥ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች። ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም። ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ ስለ ነቢያቶችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው። ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፥ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል። ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል፦ በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ። ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፥ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም። ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፥ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል። ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፥ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል። ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፥ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን። ሬስ። ስለ እርሱ፦ በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ። ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፥ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም። ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፥ ኃጢአትሽን ይገልጣል።
ሰቈቃወ 4:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቤተ መቅደስ የታነጸባቸው ድንጋዮች በየመንገዱ ተበታተኑ። ወርቁ እንዴት ደበዘዘ! ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የከበሩ የጽዮን ልጆች እንደ ንጹሕ ወርቅ ያኽል ውድ ነበሩ፤ እንዴት አሁን የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ ተቈጠሩ! ቀበሮዎች እንኳን የወለዱአቸውን ከጡታቸው ይመግባሉ፤ ሕዝቤ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጎኖች ጨካኞች ሆነዋል። በውሃ ጥም ምክንያት የሕፃናት ምላስ ከትናጋቸው ጋር ተጣበቀ፤ ልጆቻቸው ምግብ ይለምናሉ፤ ነገር ግን ምንም ነገር የሚሰጣቸው ሰው የለም። ቀደም ብለው ምርጥ ምግብ ይመገቡ የነበሩት፥ አሁን በመንገድ ላይ ወድቀዋል። ሐምራዊ ልብስ ለብሰው ያደጉት አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተጋደሙ። በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት የማንም እጅ ሳያርፍበት በቅጽበት ከተገለበጠችው ከሰዶም ቅጣት የበለጠ ነው። ልዑላን መሳፍንታችን ርኲሰት የማይገኝባቸው፥ ከበረዶ ይልቅ የጠሩ፥ ከወተትም ይልቅ የነጡ ነበሩ፤ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ያማረ ነበር፤ አሁን ግን ፊታቸው እንደ ጥላሸት ስለ ጠቈረ፥ በየመንገዱ ወድቀው ሲገኙ የሚያውቃቸው የለም፤ እንደ እንጨት የደረቀ ቆዳቸው በአጥንታቸው ላይ ተጣብቆአል። የምድር ምርትን በማጣት ቀስ በቀስ በራብ ከመሞት ይልቅ በጦርነት የሚሞቱት የተሻሉ ነበሩ። የርኅሩኅ ሴቶች እጆች የገዛ ልጆቻቸውን ቀቀሉ፤ ከተማዋ በተደመሰሰች ጊዜ እነዚያ የተቀቀሉ ልጆች ለሰዎች ምግብ ሆኑ። እግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣውን ገለጠ፤ የጽዮንን መሠረት የሚያጠፋ፥ የተቀጣጠለ እሳት የመሰለ መዓቱን አወረደ። የምድር ነገሥታትም ሆኑ የዓለም ሕዝቦች በኢየሩሳሌም የቅጽር በሮች ጠላት ይገባል ብለው አላመኑም። ይህም የሆነው በመካከልዋ የንጹሓንን ደም ባፈሰሱት በካህናትዋ በደልና በነቢያትዋ ኃጢአት ምክንያት ነው። እነርሱ በደም የረከሱ ስለ ሆኑ ሰው ልብሳቸውን እንኳ ለመንካት አይደፍርም፤ እነርሱ ግን እንደ ዕውሮች በመንገድ ላይ ይንከራተታሉ። ስለዚህም ሕዝቡ “ወዲያ ሂዱ! ስለ ረከሳችሁም አትንኩን!” እያሉ ይጮኹባቸዋል። ስለዚህ እነርሱ ስደተኞችና ተንከራታቾች ሆኑ ሕዝቦችም “ከእንግዲህ በመካከላችን አይቈዩም” አሉ። እግዚአብሔር ራሱ የበተናቸው ስለ ሆነ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ እነርሱ አያስብም፤ ለካህናቱ ክብር አይሰጣቸውም፤ ሽማግሌዎችም ልዩ አስተያየት አይደረግላቸውም። በከንቱ ረዳት በመጠበቅ ዐይናችን ደከመ ሊታደግ ከማይችል ሕዝብ በጒጒት ርዳታ ጠበቅን። ጠላትም በየመንገዱ መዘዋወር እንዳንችል በዐይነ ቊራኛ ይጠባበቀን ነበር፤ ዘመናችን ቀርቦአል፤ ዘመናችን አልቆአል፤ ፍጻሜውም ደርሶአል። አሳዳጆቻችን በሰማይ ከሚበርሩ ንስሮች የፈጠኑ ነበሩ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በበረሓም ሸመቁብን። በሕዝቦች መካከል በእርሱ ጥላ ሥር እንኖራለን ብለን ያሰብነውን እግዚአብሔር የቀባውን የሕይወት እስትንፋሳችን አጠመዱብን። እናንተ በዑፅ ምድር የምትኖሩ የኤዶም ሕዝብ ሆይ ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ! ይሁን እንጂ የእናንተም ጽዋ ተራውን ጠብቆ በመምጣት ላይ ነው፤ እናንተም ሰክራችሁ ትራቈታላችሁ። የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የበደላችሁ ቅጣት አብቅቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ በስደት እንድትኖሩ አያደርጋችሁም፤ ነገር ግን የኤዶም ሕዝብ ሆይ! የእናንተን በደል ይቀጣል፤ ኃጢአታችሁንም ያጋልጣል።
ሰቈቃወ 4:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ። ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ! ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፥ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች። ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፥ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም። ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፥ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ። ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች። ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፥ ገላቸው ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ። ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቁሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፥ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፥ ደርቆአል፥ እንደ እንጨት ሆኖአል። ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፥ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል። ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፥ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኗቸው። ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቁጣውን አፍስሶአል፥ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች። ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም። ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ ስለ ነቢዮችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው። ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፥ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል። ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል፦ በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ። ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፥ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም። ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፥ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል። ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፥ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል። ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፥ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን። ሬስ። ስለ እርሱ፦ በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጉድጓዳቸው ተያዘ። ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፥ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም። ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፥ ኃጢአትሽን ይገልጣል።