ኢያሱ 22:1-34
ኢያሱ 22:1-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ኢያሱ የሮቤልንና የጋድን ነገዶች፣ እንዲሁም የምናሴን ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ ጠብቃችኋል፤ እኔም ያዘዝኋችሁን በሙሉ ፈጽማችኋል፤ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ተልእኮ በሚገባ ተወጥታችኋል። አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ወንድሞቻችሁን አሳርፏቸዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ ርስት አድርጎ በሰጣችሁ ምድር ወዳለው ቤታችሁ ተመለሱ። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን እንድትወዱ፣ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄዱ፣ ትእዛዙን እንድትፈጽሙ፣ እርሱንም አጥብቃችሁ እንድትይዙት እንዲሁም በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት የሰጣችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ነቅታችሁ ጠብቁ።” ከዚያም ኢያሱ መርቆ አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ምድር ርስት ሰጥቷቸው ነበር፤ ለቀረው እኩሌታ ደግሞ ኢያሱ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። ኢያሱ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ባሰናበታቸው ጊዜ መረቃቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ብዙ ሀብት ይዛችሁ ማለትም አያሌ የከብት መንጋ፣ ብርና ወርቅ፣ ናስና ብረት እንዲሁም ቍጥሩ እጅግ የበዛ ልብስ ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ ከጠላት የተገኘውንም ይህን ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉት” አላቸው። ስለዚህ የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ እስራኤላውያንን ከነዓን ውስጥ ባለችው በሴሎ ትተው፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ በሙሴ አማካይነት ወደ ተቀበሏት ርስታቸው፣ ወደ ገለዓድ ምድር ተመለሱ። የሮቤልና የጋድ እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነዓን ምድር ወዳለችው፣ ዮርዳኖስ አጠገብ ወደምትገኘው ገሊሎት ወደ ተባለች ስፍራ ሲደርሱ በወንዙ አጠገብ ግዙፍ መሠዊያ ሠሩ። የእስራኤላውያን ይዞታ በሆነችው በከነዓናውያን ምድር ወሰን በገሊሎት ላይ መሠዊያ መሥራታቸውን ሌሎቹ እስራኤላውያን በሰሙ ጊዜ፣ በእነርሱ ላይ ለመዝመት የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ። ስለዚህም እስራኤላውያን የካህኑ የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን በገለዓድ ምድር ወደሚኖሩት ወደ ሮቤልና ወደ ጋድ እንዲሁም ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ላኩ፤ ከእርሱም ጋር እያንዳንዱን የእስራኤልን ነገድ የሚወክሉ ዐሥር አለቆች አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤላውያን ጐሣዎች የተውጣጡ የየቤተ ሰቡ አለቆች ነበሩ። እነርሱም በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ሄደው እንዲህ አሏቸው፤ “መላው የእግዚአብሔር ጉባኤ እንዲህ ይላል፤ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክሕደት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን ከመከተልስ እንዴት ወደ ኋላ ትላላችሁ? እንዴትስ ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችሁ ለራሳችሁ መሠዊያ ትሠራላችሁ? በፌጎር የተሠራው ኀጢአት አይበቃንምን? ምንም እንኳ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ መቅሠፍት ቢወርድም፣ እስከ ዛሬዪቱ ዕለት ድረስ ራሳችንን ከዚያች ኀጢአት አላነጻንም። እናንተ፣ አሁንም እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ትላላችሁን? “ ‘ዛሬ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ፣ እርሱ ደግሞ ነገ በመላው እስራኤል ጉባኤ ላይ ይቈጣል። የወረሳችኋት ምድር ረክሳ እንደ ሆነ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ተተከለበት ወደ እግዚአብሔር ምድር መጥታችሁ ከእኛ ጋር ርስት ተካፈሉ፤ ነገር ግን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ በስተቀር ሌላ መሠዊያ ሠርታችሁ በእግዚአብሔርም ሆነ በእኛ ላይ አታምፁ። የዛራ ልጅ አካን፣ ዕርም የሆነውን ነገር በመውሰድ ኀጢአት ስለ ሠራ፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ላይ ቍጣ አልመጣምን? በሠራው ኀጢአት የሞተውም እርሱ ብቻ አልነበረም።’ ” ከዚያም የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ጐሣ መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር! ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር! እርሱ ያውቃል! እስራኤልም ይህን ይወቅ! ይህ የተደረገው በማመፅ ወይም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ከሆነ፣ ዛሬ አትማሩን! መሠዊያውን የሠራነው እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ለማለት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ልናሳርግበት ወይም የኅብረት መሥዋዕት ልናቀርብበት አስበን ከሆነ፣ ራሱ እግዚአብሔር ይበቀለን። “እኛማ ይህን ያደረግነው፣ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ለዘሮቻችን እንዲህ እንዳይሏቸው ፈርተን ነው፤ ‘ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ? እናንት የሮቤልና የጋድ ልጆች፤ እግዚአብሔር ዮርዳኖስን በመካከላችን መለያ ድንበር ስላደረገው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም።’ ስለዚህ ዘሮቻችሁ፣ የእኛ ዘር እግዚአብሔርን እንዳይፈራ ሊያደርጉ ይችላሉ። “እኛም ‘እንነሣና መሠዊያ እንሥራ፤ የምንሠራው መሠዊያ ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይውልም’ ያልነው ለዚህ ነው። በሌላም በኩል የሚቃጠል መሥዋዕታችንን፣ ሌላውን ቍርባናችንንና የኅብረት መሥዋዕታችንን ይዘን በተቀደሰው ስፍራ እግዚአብሔርን እንደምናመልክ መሠዊያው በእኛና በእናንተ እንዲሁም በሚቀጥሉት ትውልዶች መካከል ምስክር ይሆናል። ስለዚህ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ዘሮቻችንን፣ ‘ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም’ ሊሏቸው አይችሉም። “እኛም፣ ‘ወደ ፊት እኛንም ሆነ ዘሮቻችንን እንዲህ የሚሉ ከሆነ፣ “እነሆ፤ አባቶቻችን የሠሩትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ ተመልከቱ፤ ይህ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር እንዲሆን እንጂ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይደለም” ብለን እንመልሳለን’ አልን። “በማደሪያው ድንኳን ፊት ካለው ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለእህል ቍርባን እንዲሁም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በመሥራት ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ እናምፅን? እርሱን ማምለካችንንም እንተውን? ይህ ከእኛ ይራቅ!” ካህኑ ፊንሐስና የእስራኤላውያን የጐሣ መሪዎች የነበሩት የማኅበረ ሰቡ አለቆች የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ወገኖች ያሉትን በሰሙ ጊዜ ተደሰቱ። የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም፣ የሮቤልን የጋድንና የምናሴን ወገኖች “በዚህ ነገር እግዚአብሔርን አልበደላችሁምና፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ዛሬ ዐውቀናል፤ እነሆ እስራኤላውያንን ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል” አላቸው። ከዚያም የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና መሪዎቹ፣ ከሮቤልና ከጋድ ወገኖች ጋር በገለዓድ ምድር ከተነጋገሩ በኋላ፣ ወደ ከነዓን ተመልሰው፣ ሁኔታውን ለእስራኤላውያን ነገሩ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከዚያም የሮቤልና የጋድ ወገኖች የሚኖሩበትን አገር በጦርነት ለማጥፋት የመሄድን ነገር አላነሡም። የሮቤልና የጋድ ወገኖችም፣ እግዚአብሔር አምላክ ለመሆኑ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው፤ በማለት መሠዊያውን “ምስክር” ብለው ጠሩት።
ኢያሱ 22:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፥ ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፥ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ። ኢያሱም መረቃቸው፥ ሰደዳቸውም፥ ወደ ቤታቸውም ሄዱ። ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፥ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው በሰደዳቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ መረቃቸው፦ በብዙ ብልጥግና በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፥ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ። የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሄዱ፥ በሙሴም እጅ በተሰጠ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ተቀበሉአት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ይገቡ ዘንድ በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተመለሱ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ። ለእስራኤልም ልጆች፦ እነሆ፥ በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው ግዛት፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ ሠርተዋል የሚል ወሬ ደረሰላቸው። የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ። ከእርሱም ጋር አሥር አለቆች ነበሩ፥ ከእስራኤል ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ የአባቶች ቤት አለቃ፥ እንያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የእየአባቶቻቸው ቤት አለቃ ነበረ። በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ መጡ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩአቸው፦ የእግዚአብሔር ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው፦ ይህ በእስራኤል አምላክ ላይ ያደረጋችሁት ኃጢአት ምንድር ነው? ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋል፥ ዛሬም መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል። እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ። እናንተ ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ትመለሳላችሁን? ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ይቈጣል። ነገር ግን የርስታችሁ ምድር የረከሰ ቢመስላችሁ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ እግዚአብሔር ርስት ምድር አልፋችሁ በመካከላችን ውረሱ፥ ከአምላካችንም ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለእናንተ መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔርና በእኛ ላይ አታምፁ። የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ኃጢአትን ስለ ሠራ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቁጣ አልወረደምን? እርሱም በኃጢአቱ ብቻውን አልሞተም። የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል አእላፋት አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው፦ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር፥ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር እርሱ አውቆታል፥ እስራኤልም ያውቀዋል፥ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀንና ተላልፈን እንደ ሆነ ዛሬ አታድነን፥ እግዚአብሔርን ከመከተል እንድንመለስ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቁርባን እንድናሳርግበት፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት ብለን መሠዊያ ሠርተን እንደ ሆነ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ይበቀለን፥ ይልቁንም ከልባችን ፍርሃት የተነሣ፦ በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን፦ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን አላችሁ? እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ እግዚአብሔር በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም ይሉአቸዋል ብለን ይህን አደረግን። በዚህም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን ከመፍራት ያስተዋቸዋል። ስለዚህም፦ መሠዊያ እንስራ አልን፥ ነገር ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት አይደለም፥ ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቁርባን በደኅንነትም መሥዋዕታችን እግዚአብሔርን እናመልክ ዘንድ፥ በሚመጣውም ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻንን፦ በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም እንዳይሉ ምስክር ይሆናል። ስለዚህም አልን፦ በሚመጣው ዘመን ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ እኛ፦ እነሆ፥ አባቶቻችን ያደረጉትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፥ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት አይደለም እንላለን። በማደሪያው ፊት ካለው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለእህል ቁርባን ለሌላ መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እግዚአብሔርንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደ ሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ። ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል አእላፋት አለቆች፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ልጆች የተናገሩትን ቃል በሰሙ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኛቸው። የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ልጆች፦ ይህን መተላለፍ በእግዚአብሔር ላይ አላደረጋችሁምና እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ ዛሬ እናውቃለን፥ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል አላቸው። የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና አለቆቹ ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች ዘንድ ከገለዓድ አገር ወደ ከነዓን አገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ ወሬም አመጡላቸው። ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፥ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የተቀመጡባትን ምድር ያጠፉ ዘንድ ወጥተው እንዲወጉአቸው አልተናገሩም። የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም፦ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆነ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው ሲሉ መሠዊያውን ምስክር ብለው ጠሩት።
ኢያሱ 22:1-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢያሱ የሮቤልን፥ የጋድንና በምሥራቅ ያሉትን የምናሴን ነገዶች በአንድነት ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ እንድታደርጉት ያዘዛችሁን ሁሉ ፈጽማችኋል፤ የእኔንም ትእዛዝ ሁሉ ጠብቃችኋል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ወገኖቻችሁን እስራኤላውያንን የከዳችሁበት ጊዜ የለም፤ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በጥንቃቄ ፈጽማችኋል። እነሆ አሁን አምላካችሁ እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ለወገኖቻችሁ ለእስራኤላውያን ሰላምን ሰጥቶአቸዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ወደ ሰጣችሁ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ወደሚገኘውና ርስት አድርጋችሁ ወደ ወረሳችሁት ምድር ተመልሳችሁ ሂዱ፤ ሙሴ የሰጣችሁን ሕግና ትእዛዞች በጥንቃቄ ፈጽሙ፤ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ውደዱ፤ ፈቃዱን ፈጽሙ፤ ትእዛዙንም ጠብቁ፤ ለእርሱም ታማኞች ሆናችሁ በሙሉ ልባችሁ፥ በፍጹም ሐሳባችሁ አገልግሉት።” ኢያሱም ባርኮ አሰናበታቸውና ወደ ሰፈራቸው ሄዱ፤ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሙሴ ርስት በባሳን ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለእኩሌቶቹ ደግሞ በዮርዳኖስ ምዕራብ በኩል ከወንድሞቻቸው ጋር ኢያሱ መሬት ሰጣቸው፤ ኢያሱም ባሰናበታቸው ጊዜ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “እነሆ፥ አሁን በምርኮ ያገኛችሁትን ብዙ ከብት፥ ብር፥ ወርቅ፥ ነሐስ፥ ብረትና ብዙ ልብሶች ይዛችሁ ወደ መኖሪያችሁ ልትመልሱ ስለ ሆነ ከጠላቶቻችሁ በምርኮ ያገኛችሁትን ምርኮ ከዘመዶቻችሁ ጋር ተካፈሉ።” የሮቤል፥ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነዓን ምድር በሚገኘው በሴሎ ካሉት ከእስራኤላውያን ዘንድ ተነሥተው በሙሴ አማካይነት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ተሰጣቸው ምድር ወደ ገለዓድ ተመለሱ። የሮቤል፥ የጋድና የምሥራቅ ምናሴ ነገዶች በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በከነዓን ምድር ወደሚገኘው ወደ ገሊሎት እንደ ደረሱ በወንዙ አጠገብ አስደናቂ የሆነ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ፤ የቀሩትም የእስራኤል ሕዝብ የሮቤል፥ የጋድና በምሥራቅ ያሉት የምናሴ ነገዶች በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በከነዓን ምድር በምትገኘው በእስራኤላውያን ይዞታ በሆነችው በገሊሎት መሠዊያ መሥራታቸውን ሰሙ። እስራኤላውያን ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም በአንድነት ወደ ሴሎ መጥተው በመሰብሰብ በምሥራቅ ነገዶች ላይ ሊዘምቱ ተዘጋጁ። ይህም ከመሆኑ በፊት የእስራኤል ሕዝብ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን በገለዓድ ምድር ወደሚገኙት ወደ ሮቤል፥ ወደ ጋድና በምሥራቅ ወደሚኖሩት የምናሴ ነገዶች ሕዝብ ላኩት፤ ከፊንሐስም ጋር ዐሥር ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህም እያንዳንዱ በምዕራብ ከሚገኙት ነገዶች የተውጣጡ በየጐሣቸው የቤተሰብ መሪዎች ናቸው፤ እነርሱም የሮቤል፥ የጋድና በምሥራቅ የሚኖሩት የምናሴ ሕዝብ ወደሚኖሩባት ወደ ገለዓድ ምድር መጥተው እንዲህ አሉአቸው፦ “የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚለው እንዲህ ነው፦ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ ያላችሁን እምነት እንዴት ታጓድላላችሁ? ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራት ከእግዚአብሔር ርቃችኋል፤ በእርሱም ላይ ዐምፃችኋል፤ በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት የወረደበትና እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻበት የፌጎር ኃጢአት የማይበቃን ሆኖ ነውን? እናንተስ ዛሬ እግዚአብሔርን ለመከተል እምቢ ብላችሁ በእርሱ ላይ ብታምፁ፥ እርሱ ነገ በመላው እስራኤል ላይ ይቈጣል፤ አሁን ግን ምድራችሁ የረከሰ ቢሆን የእግዚአብሔር ማደሪያ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ምድር ተሻገሩ፤ በመካከላችን ርስት ይኑራችሁ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ በመሥራት በእግዚአብሔር ላይ ወይም በእኛ ላይ አታምፁ። የዛራ ልጅ ዓካን መደምሰስ በሚገባቸው ነገሮች እምነተቢስ ሆኖ ትእዛዝ በማፍረሱ የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ላይ አልወረደምን? በጥፋቱም የጠፋው እርሱ ብቻ አልነበረም።’ ” የሮቤል፥ የጋድና በምሥራቅ የሚኖሩት የምናሴ ነገዶች ሕዝብም ለምዕራብ ነገዶች የቤተሰብ መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “ከሁሉ የሚበልጥ ኀያል እግዚአብሔር ነው! እርሱ የሁሉ ጌታ ነው! እርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ኀያል አምላክ ነው! እኛ ስለምን ይህን እንደ ሠራን እርሱ ያውቃል፤ እናንተም ስለምን እንደ ሠራነው እንድታውቁት እንፈልጋለን፤ በእውነት ካመፅንና በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት አጓድለን ከተገኘን፥ በሕይወት እንድንኖር አትፍቀዱልን፤ ለእግዚአብሔር የማንታዘዝ ከሆንንና የሠራነውን መሠዊያ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባን፥ ወይም የአንድነት መሥዋዕት ልናቀርብበት አስበን ከሆነ ራሱ እግዚአብሔር ይቅጣን፤ እኛ የሠራነው ለዚህ አይደለም፤ እኛ እርሱን የሠራነው በሚመጡት ዘመናት የእናንተ ዘሮች የእኛን ልጆች ‘እናንተ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ? እርሱ በእኛና በእናንተ፥ በሮቤልና በጋድ ሕዝቦች መካከል የዮርዳኖስን ወንዝ መለያ ድንበር አድርጎአል፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ግንኙነት አይኖራችሁም’ ይሉአቸው ይሆናል ብለን በመፍራት ብቻ ነው። በዚህም ዐይነት የእናንተ ዘሮች የእኛን ዘሮች ለእግዚአብሔር እንዳይሰግዱ ይከለክሉአቸው ይሆናል። ስለዚህ እኛ የሠራነው መሠዊያ የሚቃጠል ወይም ሌላ መሥዋዕት ለማቅረብ አይደለም። እኛ እርሱን የሠራነው በእኛና በእናንተ ሕዝብ መካከል ምልክት ሆኖ እንዲኖር ነው፤ ይኸውም ከእኛ በኋላ ለሚነሡት ትውልዶች በተቀደሰ ድንኳኑ ፊት እግዚአብሔርን እንደምናመልክ የሚቃጠልና ሌላም መሥዋዕት፥ እንዲሁም የአንድነት መሥዋዕት ስናቀርብ ለመኖራችን ምስክር ይሆናል፤ ይኸውም የእናንተ ዘሮች የእኛን ልጆች ‘ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ግንኙነት የላችሁም’ እንዳይሉአቸው ለማድረግ ይጠቅማል፤ እንግዲህ ምናልባት ይህ ነገር ቢሆን የእኛ ዕቅድ፥ ዘሮቻችን፦ ‘ተመልከቱ! የቀድሞ አባቶቻችን የሠሩት መሠዊያ ለእግዚአብሔር ከተሠራው መሠዊያ ጋር አንድ ዐይነት ነው፤ ይኸውም በእኛና በእናንተ ሕዝቦች መካከል ምልክት ሆኖ እንዲኖር እንጂ የሚቃጠል ወይም ሌላ መሥዋዕት እንዲቀርብበት ታስቦ አልነበረም’ ማለት እንዲችሉ ነው፤ እኛ በእግዚአብሔር ላይ አላመፅንም፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መባ፥ ወይም ሌላ መሥዋዕት ለማቅረብ አስበን ሌላ መሠዊያ በመሥራት እግዚአብሔርን ማምለክ አልተውንም፤ ከእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ለፊት ከቆመው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ከተሠራው ሌላ የተለየ መሠዊያ መሥራት ከእኛ ይራቅ።” ካህኑ ፊንሐስና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝቡ የላካቸው የምዕራብ ነገዶች የቤተሰብ አለቆች የሆኑት ታላላቅ ሰዎች፥ የሮቤል፥ የጋድና በምሥራቅ በሚኖሩ የምናሴ ነገዶች ሕዝብ የተናገሩትን ሰምተው መልሱ አረካቸው፤ ስለዚህም የአልዓዛር ልጅ ካህኑ ፊንሐስ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ዐወቅን፤ እናንተ በእርሱ ላይ አላመፃችሁም፤ ስለዚህም የእስራኤልን ሕዝብ ከእግዚአብሔር ቅጣት አድናችኋል።” ከዚህም በኋላ የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና መሪዎቹ በገለዓድ ከሚገኙት ከሮቤልና ከጋድ ሕዝቦች ዘንድ በከነዓን ምድር ወደሚገኙት ወደ እስራኤል ሕዝብ ተመልሰው በመምጣት፥ ያገኙትን ማስረጃ አቀረቡ፤ እስራኤላውያንም በመልሱ ረክተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከዚያም በኋላ የሮቤልና የጋድ ሕዝብ የሚኖሩባትን ምድር ለመደምሰስ ጦርነት ስለ ማንሣት ጉዳይ መናገር አልፈለጉም። የሮቤልና የጋድ ሕዝብም “ይህ መሠዊያ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ ስለ መሆኑ ለሁላችን ምስክር ነው” አሉ፤ ከዚህም የተነሣ “ምስክር” ብለው ጠሩት።
ኢያሱ 22:1-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ሰምታችኋል፤ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፤ ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፤ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። ብቻ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ እርሱንም ትከተሉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩት ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ።” ኢያሱም መረቃቸው፤ አሰናበታቸውም፤ ወደ ቤታቸውም ሄዱ። ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር በኩል በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው በአሰናበታቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ መረቃቸው፦ “በብዙ ብልጥግና፥ በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።” የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሄዱ፤ በሙሴም እጅ በተሰጠ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ተቀበሉት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ይገቡ ዘንድ በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተመለሱ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም ወደ ገለዓድ በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ የሚታይ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ። የእስራኤልም ልጆች በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው በገለዓድ፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ እንደ ሠሩ ሰሙ። የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑ የአሮንን ልጅ የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ። ዐሥር አለቆችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ አንድ አንድ የእየአባቶቻቸው ቤት አለቃ፤ እያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የአባቶቻቸው ቤት አለቃ ነበረ። በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች፥ ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ ደረሱ፤ እንዲህም ብለው ነገሩአቸው የእግዚአብሔር ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው፥ “ዛሬ እግዚአብሔርን መከተልን ትተዉ ዘንድ፥ መሠዊያም ትሠሩ ዘንድ፥ እግዚአብሔርንም ዛሬ ትክዱት ዘንድ ይህ በእስራኤል አምላክ ፊት ያደረጋችሁት ኀጢአት ምንድን ነው? እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኀጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ወረደ። እናንተ ዛሬ እግዚአብሔርን መከተልን ትታችኋል፤ ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ መቅሠፍት ይሆናል። ነገር ግን የርስታችሁ ምድር ቢያንሳችሁ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ እግዚአብሔር ርስት ምድር አልፋችሁ ከእኛ ጋር ውረሱ፤ ከአምላካችንም ከእግዚአብሔር መሠዊያ ውጭ ለእናንተ መሠዊያ ሠርታችኋልና እግዚአብሔርን አትካዱ፤ እግዚአብሔርንም አትተዉት። የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ኀጢአትን ስለ ሠራ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቍጣ አልወረደምን? እርሱም ብቻውን ቢበድል በኀጢአቱ ብቻውን ሞተን?” የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል አእላፋት አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው፦ “እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ ጌታም ነው፤ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ ነው፤ እርሱ ያውቃል። እስራኤልም ያውቀዋል። በእግዚአብሔር ፊት ያደረግነው ለበደልና ለመካድ ከሆነ ዛሬ አያድነን፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንድንክደው፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህልን ቍርባን እንድናሳርግበት፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት መሠዊያ ሠርተን እንደ ሆነ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ይመራመረን፤ ይልቁንም ከልባችን ፍርሀት የተነሣ፦ ነገ ልጆቻችሁ ልጆቻችንን፦ ከእስራኤል ልጆች አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን አላችሁ? እንዳይሉአቸው ስለፈራን ይህን የሠራነው ካልሆነ፥ እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ፥ እግዚአብሔር በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በእግዚአብሔር ዘንድ ዕድል ፋንታ የላችሁም ይሉአቸዋል፤ በዚሁም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን ከማምለክ እንዳያወጡአቸው ብለን ይህን አደረግን። ስለዚህም መሠዊያ እንሥራ አልን፤ ነገር ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለቍርባን አይደለም፤ ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል፥ ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቍርባን፥ በደኅንነትም መሥዋዕታችን እግዚአብሔርን እናመልክ ዘንድ፥ ነገ ልጆቻችሁ ልጆቻችንን፦ በእግዚአብሔር ዘንድ ዕድል ፋንታ የላችሁም እንዳይሉ ምስክር ይሆናል። ኋላ ይህ በተደረገ ጊዜ ነገ ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ፥ እኛ፦ እነሆ፥ አባቶቻችን ያደረጉትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፤ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ቍርባን አይደለም እንላለን። በድንኳኑ ፊት ካለው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለሰላም መሥዋዕት፥ ለደኅንነት መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እግዚአብሔርንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደ ሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ።” ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት የእስራኤል መሳፍንት ሁሉ ፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ የተናገሩትን ቃል በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ፤ ደስም አሰኛቸው። የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ነገድ እኩሌታ፥ “ይህን መተላለፍ በእግዚአብሔር ላይ አላደረጋችሁምና እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ ዛሬ እናውቃለን፤ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል” አላቸው። የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ከእርሱም ጋር የማኅበሩ አለቆች ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ዘንድ ከገለዓድ ሀገር ወደ ከነዓን ሀገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፤ ወሬም አመጡላቸው። ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፤ ለእስራኤልም ልጆች በነገሩአቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ የተቀመጡባትን ምድር ያጠፉ ዘንድ ለመውጋት አንወጣም ተባባሉ። ኢያሱም መሠዊያውን “የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ምስክር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆነ ይህ በመካከላቸው ምስክር ነውና።
ኢያሱ 22:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች፥ የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፤ ይህንንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የጌታን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። እንግዲህ አሁን አምላካችሁ ጌታ እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ ስለዚህ አሁን ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የጌታ ባርያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። ብቻ የጌታ ባርያ ሙሴ አምላካችሁን ጌታን እንድትወድዱ፥ መንገዱንም ሁሉ እንድትሄዱ፥ ትእዛዙንም እንድትጠብቁ፥ እርሱንም በጽኑ እንድትይዙት፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ እንድታገለግሉት ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን በጥንቃቄ አድርጉ።” ኢያሱም ባረካቸው፥ እንዲሄዱም አሰናበታቸው፤ ወደ ቤታቸውም ሄዱ። ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው ባሰናበታቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “በብዙ ሀብት እጅግም ብዙ በሆነ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ እጅግም ብዙ በሆነ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።” የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በሙሴ አማካይነት በተሰጠ በጌታ ትእዛዝ ወደ ተቀበሉአት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ለመግባት በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተለይተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ። የእስራኤልም ልጆች እንዲህ የሚል ወሬ ሰሙ፦ “እነሆ፥ በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው ግዛት፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ ሠርተዋል።” የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ። ከእርሱም ጋር ዐሥር አለቆች ነበሩ፥ ከእስራኤል ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ የአባቶች ቤት አለቃ፤እንያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የእየአባቶቻቸው ቤት አለቆች ነበሩ። በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ መጡ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩአቸው፦ “የጌታ ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው፦ ‘ዛሬ ጌታን ከመከተል በመመለሳችሁ፥ መሠዊያም ሠርታችሁ ዛሬ በጌታ ላይ በማመፃችሁ ይህ በእስራኤል አምላክ ላይ ያደረጋችሁት አለመታመን ምንድነው? በጌታ ማኅበር ላይ መቅሰፍት ያወረደውና እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? እናንተ ዛሬ ጌታን ከመከተል ትመለሳላችሁን? ዛሬ በጌታ ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ይቈጣል። ነገር ግን የርስታችሁ ምድር የረከሰ ቢመስላችሁ የጌታ ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ ጌታ ርስት ምድር አልፋችሁ በመካከላችን ውረሱ፤ ከአምላካችንም ከጌታ መሠዊያ ሌላ ለእናንተ መሠዊያ በመሥራታችሁ በጌታና በእኛ ላይ አታምፁ። የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ስላልታመነ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቁጣ አልወረደምን? እርሱም በበደሉ ብቻውን አልሞተም።’ ” የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ነገድ አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው፦ “የአማልክት አምላክ ጌታ! የአማልክት አምላክ ጌታ! እርሱ አውቆታል፥ እስራኤልም ራሱ ይወቀው፤ በጌታ ላይ ዐምፀንና ተላልፈን እንደሆነ ዛሬ አታድነን፤ ጌታን ከመከተል እንድንመለስ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቁርባን እንድናሳርግበት፥ የአንድነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት ብለን መሠዊያ ሠርተን እንደሆነ ጌታ እርሱ ራሱ ይበቀለን፤ ይልቁንም ይህን ያደረግነው ከልባችን ፍርሃት የተነሣ ሲሆን እንዲህም አልን፦ በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን፦ ‘ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ጋር ምን ነገር አላችሁ? እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ ጌታ በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በጌታ ዘንድ ድርሻ የላችሁም ይሉአቸዋል።’ በዚህም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን ጌታን እንዳይፈሩ ያደርጓቸዋል። ስለዚህም፦ ‘ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ያልሆነን መሠዊያ እንስራ አልን፤ ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቁርባን በአንድነትም መሥዋዕታችን ጌታን እንድናገለግል፥ በሚመጣውም ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻንን፦ “በጌታ ዘንድ ድርሻ የላችሁም” እንዳይሉ ምስክር ይሆናል።’ ስለዚህም እንዲህ አልን፦ በሚመጣው ዘመን ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ እኛ እንዲህ እንላለን፦ ‘እነሆ፥ አባቶቻችን የሠሩትን የጌታን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፤ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለማቅረብ አይደለም።’ በማደሪያው ፊት ለፊት ካለው ከአምላካችን ከጌታ መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለእህል ቁርባን ለሌላ መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በጌታ ላይ በማመፅ ጌታንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ።” ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል ነገድ አለቆች፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ልጆች የተናገሩትን ቃላት በሰሙ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኛቸው። የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “ይህን መተላለፍ በጌታ ላይ አላደረጋችሁምና ጌታ በመካከላችን እንዳለ ዛሬ አውቀናል፤ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከጌታ እጅ አድናችኋል።” የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና አለቆቹ ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች ዘንድ ከገለዓድ አገር ወደ ከነዓን አገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ ወሬም ይዘውላቸው መጡ። ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፤ የእስራኤልም ልጆች ጌታን አመሰገኑ፥ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የተቀመጡባትን ምድር ለማጥፋት ወጥተን እንወጋታለን ብለው አልተናገሩም። የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም፦ “ጌታ አምላክ እንደሆነ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው” ሲሉ መሠዊያውን ምስክር ብለው ጠሩት።