የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 22

22
1በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ 2የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፥ 3ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። 4አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፥ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። 5ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ። 6ኢያሱም መረቃቸው፥ ሰደዳቸውም፥ ወደ ቤታቸውም ሄዱ።
7ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፥ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው በሰደዳቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ መረቃቸው፦ 8በብዙ ብልጥግና በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፥ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።
9የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሄዱ፥ በሙሴም እጅ በተሰጠ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ተቀበሉአት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ይገቡ ዘንድ በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተመለሱ። 10በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ። 11ለእስራኤልም ልጆች፦ እነሆ፥ በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው ግዛት፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ ሠርተዋል የሚል ወሬ ደረሰላቸው። 12የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ።
13የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ። 14ከእርሱም ጋር አሥር አለቆች ነበሩ፥ ከእስራኤል ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ የአባቶች ቤት አለቃ፥ እንያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የእየአባቶቻቸው ቤት አለቃ ነበረ። 15በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ መጡ፥ 16እንዲህም ብለው ተናገሩአቸው፦ የእግዚአብሔር ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው፦ ይህ በእስራኤል አምላክ ላይ ያደረጋችሁት ኃጢአት ምንድር ነው? ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋል፥ ዛሬም መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል። 17እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ። 18እናንተ ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ትመለሳላችሁን? ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ይቈጣል። 19ነገር ግን የርስታችሁ ምድር የረከሰ ቢመስላችሁ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ እግዚአብሔር ርስት ምድር አልፋችሁ በመካከላችን ውረሱ፥ ከአምላካችንም ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለእናንተ መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔርና በእኛ ላይ አታምፁ። 20የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ኃጢአትን ስለ ሠራ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቁጣ አልወረደምን? እርሱም በኃጢአቱ ብቻውን አልሞተም።
21የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል አእላፋት አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው፦ 22የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር፥ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር እርሱ አውቆታል፥ እስራኤልም ያውቀዋል፥ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀንና ተላልፈን እንደ ሆነ ዛሬ አታድነን፥ 23እግዚአብሔርን ከመከተል እንድንመለስ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቁርባን እንድናሳርግበት፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት ብለን መሠዊያ ሠርተን እንደ ሆነ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ይበቀለን፥ 24ይልቁንም ከልባችን ፍርሃት የተነሣ፦ በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን፦ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን አላችሁ? 25እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ እግዚአብሔር በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም ይሉአቸዋል ብለን ይህን አደረግን። በዚህም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን ከመፍራት ያስተዋቸዋል። 26ስለዚህም፦ መሠዊያ እንስራ አልን፥ ነገር ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት አይደለም፥ 27ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቁርባን በደኅንነትም መሥዋዕታችን እግዚአብሔርን እናመልክ ዘንድ፥ በሚመጣውም ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻንን፦ በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም እንዳይሉ ምስክር ይሆናል። 28ስለዚህም አልን፦ በሚመጣው ዘመን ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ እኛ፦ እነሆ፥ አባቶቻችን ያደረጉትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፥ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት አይደለም እንላለን። 29በማደሪያው ፊት ካለው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለእህል ቁርባን ለሌላ መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እግዚአብሔርንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደ ሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ።
30ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል አእላፋት አለቆች፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ልጆች የተናገሩትን ቃል በሰሙ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኛቸው። 31የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ልጆች፦ ይህን መተላለፍ በእግዚአብሔር ላይ አላደረጋችሁምና እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ ዛሬ እናውቃለን፥ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል አላቸው። 32የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና አለቆቹ ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች ዘንድ ከገለዓድ አገር ወደ ከነዓን አገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ ወሬም አመጡላቸው። 33ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፥ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የተቀመጡባትን ምድር ያጠፉ ዘንድ ወጥተው እንዲወጉአቸው አልተናገሩም። 34የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም፦ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆነ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው ሲሉ መሠዊያውን ምስክር ብለው ጠሩት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ