ዮናስ 1:3-6
ዮናስ 1:3-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይሸሽ ዘንድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፤ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ። እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ፤ በባሕሩም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ፤ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። መርከበኞቹም ፈሩ፤ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱም እንድትቀልልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ ተኝቶም ያንኳርፍ ነበር። የመርከቡም አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፥ “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” አለው።
ዮናስ 1:3-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ኰበለለ፤ ወደ ተርሴስም ለመሄድ ተነሣ። ወደ ኢዮጴ ወረደ፤ ወደዚያው ወደ ተርሴስ የምትሄድ መርከብም አገኘ። የጕዞውንም ዋጋ ከከፈለ በኋላ፣ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ለመኰብለል በመርከቢቱ ተሳፈረ። እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን ላከ፤ ከባድ ማዕበልም ተነሥቶ መርከቢቱን አንገላታት፤ ልትሰበርም ተቃረበች። መርከበኞቹ ሁሉ ፈሩ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደ አምላኩ ጮኸ፤ የመርከቢቱም ክብደት እንዲቀልል፣ በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕሩ ጣሉት። ዮናስ ግን ወደ መርከቢቱ ታችኛ ክፍል ወርዶ ተኛ፤ በከባድም እንቅልፍ ላይ ነበር። የመርከቢቱም አዛዥ ወደ እርሱ ሄዶ፣ “እንዴት ትተኛለህ? ተነሥና አምላክህን ጥራ እንጂ፤ ምናልባትም ያስበንና ከጥፋት ያድነን ይሆናል” አለው።
ዮናስ 1:3-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ለመኰብለል አስቦ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወርዶ ከዚያ ወደ ተርሴስ የምትጓዝ መርከብ አገኘ፤ ለጒዞ የሚያስፈልገውንም ዋጋ ከከፈለ በኋላ ወደ መርከቢቱ ገባ፤ ሐሳቡም ከእግዚአብሔር ለመሸሽ ነበር። እግዚአብሔር ግን በባሕሩ ላይ ከባድ ነፋስን አስነሣ፤ በባሕሩም ላይ የተቀሰቀሰው ማዕበል ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ መርከቢቱ ልትሰበር ተቃረበች፤ መርከበኞቹም እጅግ ስለ ፈሩ እያንዳንዱ ወደ አምላኩ ጮኸ፤ የመርከቢቱን ክብደት ለመቀነስ አስበው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ እያወጡ ወደ ባሕር ጣሉ፤ ዮናስ ግን በመርከቢቱ ታችኛ ክፍል ወርዶ በመተኛቱ በከባድ እንቅልፍ ላይ ነበር። የመርከብ አዛዡም ወደ እርሱ ቀርቦ “እንዴት ትተኛለህ? ኧረ እባክህ ተነሥና ወደ አምላክህ ጸልይ፤ ምናልባት ራርቶልን ሕይወታችንን ያድን ይሆናል” አለው።
ዮናስ 1:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዮናስ ግን ከጌታ ፊት ወደ ተርሴስ ለመሸሽ ተነሣ፤ ወደ ያፎም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምትሄድ መርከብ አገኘ፤ ከጌታ ፊት ሸሽቶ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ለመሄድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ ገባ። ጌታ ግን በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አስነሣ፥ በባሕሩም ላይ ታላቅ ማዕበል ተነሣ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱ እንዲቀልልላቸውም መርከቢቱ ውስጥ የነበሩትን ዕቃዎች ወደ ባሕር ጣሉ፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ታችኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር። የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ “እንዴት ትተኛለህ? ተነሥ አምላክህን ጥራ፥ ምናልባትም እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን ይሆናል” አለው።