ዮሐንስ 8:1-20
ዮሐንስ 8:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። በጥዋትም ገስግሦ ዳግመኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ እርሱም ተቀምጦ ያስተምራቸው ጀመር። ጻፎችና ፈሪሳውያንም በዝሙት የተያዘች ሴት ወደ እርሱ አምጥተው በመካከል አቆሙአት። እንዲህም አሉት፥ “መምህር ሆይ፥ ይቺን ሴት ስታመነዝር አግኝተን ያዝናት። እንደዚችም ያለችው በድንጋይ እንድትደበደብ ሙሴ በኦሪት አዘዘን፤ እንግዲህ አንተ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” በእርሱም ላይ ምክንያት ሊያገኙ ሲፈትኑት ይህን አሉ፤ ጌታችን ኢየሱስም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። ብዙ ጊዜ መላልሰው በጠየቁት ጊዜም ዐይኖቹን አንሥቶ፥ “ከእናንተ ኀጢኣት የሌለበት አስቀድሞ ድንጋይ ይጣልባት” አላቸው። ዳግመኛም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ኅሊናቸው ወቅሶአቸው ከሽማግሌዎች ጀምሮ እስከ ኋለኞቹ ድረስ፥ አንዳንድ እያሉ ወጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፤ ሴትዮዪቱም በመካከል ቆማ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ቀና ብሎ ወደ እርስዋ ተመለከተና እንዲህ አላት፥ “አንቺ ሴት፥ የሚከሱሽ ወዴት አሉ?” እርስዋም፥ “ጌታ ሆይ፥ የማየው የለም” ብላ መለሰችለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ ኀጢኣት አትሥሪ” አላት። ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ፥ “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም፥ “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ እንግዲያስ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ ስለራሴ ብመሰክርም ምስክርነቴ እውነት ነው፤ ከየት እንደመጣሁ፥ ወዴት እንደምሄድም አውቃለሁና፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወዴት እንደምሄድም አታውቁም። እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ ግን በማንም አልፈርድም። እኔ ብፈርድም እውነትን እፈርዳለሁ፤ እኔና የላከኝ አብ ነን እንጂ አንድ ብቻዬን አይደለሁምና። የሁለት ሰዎች ምስክርነት የታመነ እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። እኔ ስለ ራሴ ምስክር ነኝ፤ የላከኝ አብም ይመሰክርልኛል።” እነርሱም፥ “አባትህ የት ነው?” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔን አታውቁም፤ አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር” ብሎ መለሰላቸው። ጌታችን ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ሲያስተምራቸው በሙዳየ ምጽዋት አጠገብ ይህን ተናገራቸው፤ ነገር ግን አልያዙትም፤ ጊዜው ገና አልደረሰም ነበርና።
ዮሐንስ 8:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። በማለዳም በቤተ መቅደስ አደባባይ እንደ ገና ታየ፤ ሕዝቡም በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ሊያስተምራቸውም ተቀመጠ። የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በምንዝር የተያዘች ሴት አመጡ፤ በሕዝቡም ፊት አቁመዋት፣ ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር ተያዘች፤ ሙሴም፣ እንደዚች ያሉ ሴቶች በድንጋይ እንዲወገሩ በሕጉ አዝዞናል፤ አንተስ ምን ትላለህ?” ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት፣ እርሱን የሚከስሱበት ምክንያት ለማግኘት ሲፈትኑት ነው። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ጀመር። በጥያቄ ሲወተውቱት ቀና ብሎ፣ “ከእናንተ ኀጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” አላቸው። እንደ ገናም ጐንበስ ብሎ በምድር ላይ ጻፈ። ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች። ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት። ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው። ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምትመሰክር ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም። እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤ ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው። የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።” ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግቢ፣ በግምጃ ቤት አጠገብ ሲያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።
ዮሐንስ 8:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው፦ “መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” አሉት። የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፦ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸዋና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፦ “አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርስዋም፦ “ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ” አለች። ኢየሱስም፦ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” አላት። ደግሞም ኢየሱስ፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም፦ “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ “እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም። እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም። የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ትጽፎአል። ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” እንግዲህ፦ “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ “እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር” አላቸው። ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተም በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም።
ዮሐንስ 8:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ተመልሶ መጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ተቀምጦ ያስተምር ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ስታመነዝር የተያዘች ሴት አመጡና በሕዝቡ መካከል አቆሙአት። ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፦ “መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተይዛለች፤ እንዲህ ዐይነትዋ ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ሙሴ በሕጋችን አዞናል፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” ይህንንም ያሉት በእርሱ ላይ የክስ ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ፈልገው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በመሬት ላይ ይጽፍ ጀመር። ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ ቀና አለና፥ “ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ በእርስዋ ላይ ይጣል!” አላቸው። ከዚህም በኋላ እንደገና ጐንበስ ብሎ በመሬት ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጀምሮ ሁሉም አንድ በአንድ ከዚያ ሄዱ፤ ስለዚህ ኢየሱስ በመካከል ቆማ ከነበረችው ሴት ጋር ብቻውን ቀረ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ቀና ብሎ፥ “አንቺ ሴት ከሳሾችሽ የት አሉ? የፈረደብሽ ማንም የለምን?” አላት። እርስዋም “ጌታ ሆይ! ማንም የለም” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ዳግመኛ ኃጢአት አትሥሪ” አላት። እንደገናም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል፤ በጨለማም አይመላለስም” ሲል ተናገራቸው። ፈሪሳውያን “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ምንም እንኳ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁ፥ ወዴትም እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም። እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም። ብፈርድም እንኳ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነና እኔ ብቻዬን ስለማልፈርድ ፍርዴ እውነት ነው፤ የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። ስለዚህ እኔ ስለ ራሴ እመሰክራለሁ፤ የላከኝ አብም ስለ እኔ ይመሰክራል።” በዚያን ጊዜ እነርሱ “አባትህ የት አለ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ይህን ቃል የተናገረው በቤተ መቅደስ በገንዘብ መቀበያ ሣጥን አጠገብ ሆኖ ሲያስተምር ነው። ታዲያ፥ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።
ዮሐንስ 8:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ ግን ወደ ደብረዘይት ሄደ። ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ፤ በመካከልም እርሱዋን አቁመው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ! ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርሷ ምን ትላለህ?” የሚከሱበትን ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህንን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት፤” አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፤ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ኢየሱስም ቀና ብሎ “አንቺ ሴት! ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም “ጌታ ሆይ! አንድም እንኳን፤” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ፤” አላት። ደግሞም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም፤” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ስለ እራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድምሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንደምሄድ አታውቁም። እናንተ በሥጋዊ መንገድ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ላይ እንኳ አልፈርድም። የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነውና፥ ብቻዬንም አይደለሁምና፥ እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደሆነ በሕጋችሁ ትጽፎአል። ስለ እራሴ የምመሰክረው እኔ ነኝ፤ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” ስለዚህም “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔንም ሆነ አባቴንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፤” አላቸው። ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህንን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም።